መስከረም 27/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) በኢትዮጵያ በመጀመሪያ ደረጃ ክብካቤ ዘርፍ ዓለም አቀፍ ተቋማት ድጋፍ በመቀነሱ ምክንያት፤ የፋይናንስ እና የግብዓት እጥረት ፈታኝ መሆኑን ጤና ሚኒስቴር ገልጿል፡፡
መንግሥት ይህንን ችግር ለመቀነስ ለዘርፉ ከፍተኛ በጀት በመመደብ እንዲሁም፤ ሀገር በቀለ ግብዓቶችን በመጠቀም ለችግሮች መፍትሔ ለመሰጠት እየሰራ እንደሚገኝ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ለአሐዱ አስታውቋል።
ታች ላለው ሕብረተሰብ የጤና ግብዓቶችን ለማድረስ እንዲሁም አገልግሎት ለመስጠት የፋይናንስ ዕጥረት ችግር መሆኑን ለአሐዱ የተናገሩት፤ የጤና ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ዳይሬክተር ጀነራል መብራቱ ማሴቦ ናቸው።
ኢትዮጵያ ባለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት የማኅበረሰቡን ጤና የሚያሻሽሉ ሥራዎችን ስትተገብር በመቆየቷ፤ የእናቶችን የወሊድ ሞት ምጣኔ በመቀነስ እና የጤና ተቋማት ተደራሽነትን በማስፋፋት ሥራ የመጀመሪያ ደረጃ ጤና ክብካቤ አስተዋጽኦ የጎላ ስለመሆኑ ጠቁመዋል።
የጤና ሚኒስቴር ከዓለም አቀፉ የመጀመሪያ ደረጃ ጤና ክብካቤ ጋር ባለፉት ዓመታት በኢትዮጵያ የመጀመሪያ ደረጃ ጤና ክብካቤን ለማኅበረሰቡ ተደራሽ ለማድረግ በመቀናጀት ሲተገበር መቆየቱን አብራርተዋል።
ለዘርፉ በመንግሥት ከተመደበው 80 በመቶ በጀት ለዚህ አገልግሎት መዋሉን የገለጹት የጽሕፈት ቤት ኃላፊ ዳይሬክተሩ፤ መሰል ሥራዎች ቢሰሩም ያሉ ችግሮችን ሙሉ በሙሉ ማስቀረት እንዳልተቻለ ነግረውናል።
ለጤናው ዘርፍ የሚመደበው በጀት ባለፉት ዓመታት እየጨመረ ቢመጣም፤ ከዓለም አቀፍ ስምምነቶች አንጻር ሲታይ መጠኑ "ዝቅተኛ" መሆኑን ተናግረዋል።
ይህንን ለመቅረፍ በመረጃ ላይ የተመሠረተ የጤና ሥርዓትን መገንባት፣ የውስጥ ፖሊሲዎችን ማሻሻል፣ የጤና ባለሙያዎችን አቅም ማጎልበት እና ማኅበረሰብ ተኮር የጤና ተደራሽነትን ማስፋት ላይ ውጤታማ ሥራ እየተሰራ ነው ብለዋል።
የመጀመሪያ ደረጃ ጤና ክብካቤ ለአንድ ሀገር የጤና ስርዓት ወሳኝ ከሆኑ ሥራዎች መካከል መሆኑን ተናግረዋል።
የመጀመሪያ ደረጃ ጤና ክብካቤ ጠንካራ፣ ፍትሃዊና ሰዎችን መሰረት ያደረገ የጤና ስርዓት መዘርጋት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
በጤናው ዘርፍ ከሚሰሩ የመንግሥትና የግል ተቋማት እንዲሁም፤ ምሁራን ጋር በመተባበር ዘርፉን ለማጠንከር እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ባለፉት ሃያ ዓመታት የዜጎችን ጤና የሚያሻሽሉ ሥራዎችን ተግባራዊ ስታደርግ መቆየቷን ጠቁመው፤ በዚህም በዓለም አቀፍ ደረጃ የተሻለ ደረጃ ላይ እንድትሆን ማስቻሉን አስታውሰዋል።
በዚህም ሂደት የእናቶችን የወሊድ ሞት ምጣኔ በመቀነስ እና የጤና ተቋማት ተደራሽነትን በማስፋፋት ሥራ የመጀመሪያ ደረጃ ጤና ክብካቤ አስተዋጽኦ የጎላ ስለመሆኑ አሳስበዋል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
የመጀመሪ ደረጃ ጤና ክብካቤ ለማስቀጠል የፋይናንስና እና የግብዓት እጥረት ፈታኝ መሆናቸውን ጤና ሚኒስቴር ገለጸ
