መስከረም 27/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) የአፍሪካ አቅም ግንባታ ፋውንዴሽን (ACBF) "ትኩረት በአፍሪካ የግብር እና ፋይናንስ አስተዳደር ክፍተት ማጥበብ ላይ" በሚል መሪ ቃል 34ተኛ ዓመታዊ ጉባኤውን በዛሬው ዕለት በአዲስ አበባ ሸራተን አዲስ ሆቴል ማካሄድ ጀምሯል፡፡

የፋይናንስ ሚኒስትሮችን እና ከፍተኛ የፖሊሲ አውጪዎችን ያሰባሰበው ይህ ጉባኤ፤ አፍሪካ የሀገር ውስጥ የገቢ ምንጮችን በማጠናከር ልማቷን በራሷ አቅም ለመምራት የሚያስችላትን የስትራቴጂ አቅጣጫዎች ለመቀየስ ያለመ ነው።

የዘንድሮው ስብሰባ መሪ ሃሳብ "ከግብር አሰባሰብ ወደ ተግባር፤ በአፍሪካ የሕዝብ ፋይናንስ አስተዳደር የፖሊሲ እና ትግበራ ክፍተትን ማገናኘት" የተሰኘ ሲሆን፤ የአፍሪካ ሀገራት የፋይናንስ ፖሊሲዎቻቸውን ወደ ተጨባጭ የልማት ተግባራት ለመለወጥ የሚችሉባቸውን መንገዶች ላይ ትኩረት ያደርጋል።

በዚህም በመሠረት በዛሬው ዕለት የመሪዎች ቦርድ ስብሰባ የተካሄደ ሲሆን፤ በስብሰባው መክፈቻው ላይ የኮትዲቯር የፋይናንስ ሚኒስትር እና የመሪዎች ቦርድ ሊቀመንበር አዳማ ኩሊባሊ፣ የሥራ አስፈጻሚ ቦርድ ሊቀመንበር አቶ መሀመድ ቤአቮጊ እና የስብሰባው አስተናጋጅ የኢትዮጵያ ፋይናንስ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ የመክፈቻና የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር አድርገዋል።

Post image

የአፍሪካ ልማት ባንክ፣ የአፍሬክሲም ባንክ እና የአፍሪካ ሕብረትን ጨምሮ፤ ከተለያዩ አጋር ተቋማት የተውጣጡ ልዑካንም የመልካም ምኞት መልዕክቶችን አስተላልፈዋል።

በመድረኩ በተካሄደው የልምድ ልውውጥ ላይም፤ "በሀገር ውስጥ የሀብት ማሰባሰብ የጤና ፋይናንስን ማስቀጠል፣ የጤና ግብሮች በሕዝብ ፋይናንስ አስተዳደር ማሻሻያዎች ውስጥ ስላላቸው ስትራቴጂያዊ ሚና" የሚለው ርዕስ ትኩረት ተሰጥቶበታል።

በዚህ ዙሪያ ከኬፕ ታውን ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር ኮርኔ ቫን ዋልቢ ባደረጉት ገለጻ፤ በአፍሪካ የሕዝብ ፋይናንስ አስተዳደር ማሻሻያ ውስጥ ለልማት የሚውል ሀብት ለማሰባሰብ የጤና ግብሮችን የመጠቀም ፋይዳ የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።

ይህ የመሪዎች ቦርድ ስብሰባ ቀጥሎ ከጥቅምት 8 እስከ 10 ቀን 2018 ዓ.ም. ድረስ 11ኛው የአፍሪካ የጥናትና ምርምር ተቋማት ጉባኤ (Africa Think Tank Summit) እንደሚካሄድ ተመላክቷል።

በዚህ ትልቅ ጉባኤ ከ500 በላይ ተሳታፊዎች እና 50 የአፍሪካ የጥናት ተቋማት ተወካዮች እንደሚገኙ ይጠበቃል።

ጉባኤው የሀገር ውስጥ የሀብት ማሰባሰብን ማጠናከር ላይ በማተኮር፤ ለአፍሪካ የልማት አጀንዳ 2063 መሳካት የፖሊሲ መፍትሄዎችን ለመቀየስ ያለመ ነው ተብሏል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ