መስከረም 20/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) ‎በየጊዜው የሚያጋጥመውን የመድኃኒት አቅርቦት እጥረት ለመፍታት፤ በሀገር ውስጥ የሚመረቱ መድኃኒቶች ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መሆኑን የኢትዮጵያ ጤና መድኅን አገልግሎት አስታውቋል።

ይህኛው የአገልግሎቱ እርምጃ በአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች ዘንድ በተደጋጋሚ የሚነሱትን ቅሬታዎች ለመቀነስ የሚደረገው ጥረት አካል መሆኑን የተናሩት፤ በአገልግሎቱ የአባላት አስተዳደር እና ሀብት አሰባሰብ መሪ ሥራ አስፈፃሚ አቶ ጉደታ አበበ ናቸው፡፡

የመድኃኒት አቅርቦት እጥረት ችግር በየጊዜው የሚነሳ መሆኑን ለአሐዱ የገለጹት አቶ አበበ፤ ቅሬታውን በተያዘው በጀት ዓመት ሙሉ ለሙሉ መፍታት ባይቻልም ለመቀነስ የሚያስችሉ ተግባራት ተጀምረዋል ብለዋል።

የመድኃኒት አቅርቦት ችግርን በዘላቂነት ለመፍታት እና የዜጎችን ጤና መድኅን አገልግሎት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ከተደረጉ ጥረቶች መካከል፤ የመድኃኒት መደብሮችን መክፈትን ጨምሮ ከጤና ሚኒስቴር ጋር የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

የመድኃኒት አቅርቦትን ለማሻሻል በዋናነት የተወሰደው አማራጭ በሀገር ውስጥ የሚመረቱ መድኃኒቶችን የማሳደግ እና አቅርቦታቸውን ማረጋገጥ መሆኑን አቶ ጉደታ አበበ አብራርተዋል።

ፈዋሽነታቸው የተረጋገጠ በሀገር ውስጥ የሚመረቱ መድኃኒቶች ቁጥር መብዛት የውጭ ምንዛሪ ጥገኝነትን ከመቀነስ ባለፈ፣ የአቅርቦት ሰንሰለት መስተጓጎል ሲከሰት ሊፈጠር የሚችለውን የመድኃኒት እጥረት መከላከል እንደሚያስችልም መሪ ስራ አስፈጻሚው ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ከዚህ ቀደም ስምንት በመቶ የነበረው የሀገር ውስጥ መድኃኒት አምራቾች የማምረት አቅም፤ 30 በመቶ መድረሱን ማስታወቁ የሚታወስ ነው፡፡

አገልግሎቱ ከግንቦት 26 ቀን 2017 ጀምሮ ሥራ ላይ የዋለው መመሪያ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችን የሚያበረታታ መሆኑን ገልጾ፤ በመመሪያው መሠረት የሀገር ውስጥ የማምረት አቅምን በማሳደግ እንደ ሀገር 60 በመቶ የሚሆነውን የመድኃኒት ፍጆታ በሀገር ውስጥ ምርት ለመሸፈን እቅድ መያዙንም አስታውቋል፡፡

በኢትዮጵያ የ2017 በጀት ዓመት በመንግሥት እና በግል ጤና ተቋማት ለነበረው የመድኃኒት አቅርቦት በአጠቃላይ ከ1 ነጥብ 1 ቢሊየን ዶላር በላይ ወጪ መደረጉን የኢትዮጵያ መድኃኒት ምርት እና የሕክምና መገልገያ አምራቾች ማህበር ለአሐዱ መግለጹ ይታወሳል፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ