መስከረም 20/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) በግንባታ ሥራ ወቅት በሚፈጠር አደጋ ሕይወታቸው ከሚያልፍ ሠራተኞች ውስጥ የአብዛኞቹ መረጃዎች ሳይታወቁና ለፖሊስ ሪፖርት ሳይደረጉ እንደሚቀሩ፤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን ለአሐዱ አስታውቋል።

ከ2015 ዓ.ም እስከ ግንቦት 24 ቀን 2017 ዓ.ም. ድረስ ብቻ በሕንፃ ሥራ ላይ እያሉ በተለያየ ምክንያ 121 ወንዶች እና 21 ሴቶች በአጠቃላይ 142 ሰዎች ሕይወታቸው ማለፉን፤ የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ኢንጅነር ሕይወት ሳሙኤል ተናግረዋል።

እነዚህ ቁጥሮች ግን በተገቢው ሁኔታ የተመዘገቡና ከፖሊስ ሪከርድ የተገኙት ብቻ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ከዚህ ውጪ መረጃውን ለፖሊስ ሳያሳውቁ ባለበት ተዳፍኖ የሚቀርና በሽምግልና ብቻ እንዲያልቁ የሚደረጉ በርካታ ዳታዎች መኖራቸውን ጠቁመዋል።

በዚህም መሠረት በግንባታ ሥራ ላይ ሕይወታቸው የሚያልፉ ሰዎች ለፖሊስ ሪፖርት ከሚደረገው በላይ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው መሆኑን ገልጸው፤ በዚህ ጉዳይ ተጨማሪ የተጠናከረ ሥራ እንደሚሰራበት አስታውቀዋል።

ሪፖርት የማይደረጉ የአደጋ መረጃዎችን በመተለከተ አሰሪዎች ወይም ባለቤቶች ላይ ቅጣት የሚጥል ሕግ መኖሩን ያነሱት ዋና ዳይሬክተሯ፤ ከወንጀል ጋር የተገናኘውን ጉዳይ ፖሊስ ተፈፃሚ እንደሚያደርገው ተናግረዋል።

ከዚህ ውጪ ግን የሕንፃ ደህንነትን ባለመጠበቅና ጥንቃቄ ባለማድረግ ለሚፈጠር አደጋ በወንጀለኛ መቅጫ እና በኮንስትራክሽን ሕጉ መሠረት የሚያስቀጣ መሆኑን ገልጸዋል።

ለአብነትም በግንባታ ወቅት መውሰድ የሚገባቸውን የጥንቃቄ እርምጃዎች አለመውሰድ እንደየ እርከኑ እስከ 50 ሺሕ ብር የገንዘብ ቅጣት እንደሚያስቀጣ አስታውቀዋል።

በተጨማሪም የሕንፃዎችን ደህንነት አስጠብቆ የሠራተኞችን ጉዳት ከመቀነስ አንፃር በዘርፉ ከተሰማሩ አካላት ጋር በመተባበር በስፋት እየተሰራበት እንደሚገኝ ገልጸው፤ በቅርቡም አደገኛ የደህንነት ስጋት ያለባቸው 3 ሺሕ 544 ሕንፃዎች መለየታቸውን ተናግረዋል።


ከእነዚህም ውስጥ 2 ሺሕ 948 የሚሆኑትን የገንዘብ ቅጣት በመቅጣትና ግንዛቤ በመፍጠር ቢያንስ ትንሹን የደህንነት መስፈርት እንዲያሟሉ መደረጉን ገልጸዋል።

Post image

የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራ ተቋራጮች ማህበር ፕሬዚዳንት ኢንጅነር የሱፍ መሀመድ በበከሉላቸው፤ በጥንቃቄ ጉድለትና በቸልተኝነት ምክንያት በግንባታ ሥራ ወቅት ሕይወታቸው የሚያልፍ በርካታ ሰዎች መኖራቸውን ተናግረዋል።

መረጃዎች ሪፖርት አለመደረጋቸው ምን ያክል አደጋ እየደረሰ እንደሆነና በምን ምክንያት እንደተከሰተ እንዲሁም፤ መፍትሄ ለመውሰድ ምን መደረግ አለበት? ተብሎ ለመስራት አስቸጋሪ እንደሆነ ገልጸዋል።

ስለዚህ በተገቢው መንገድ ችግሩን መቅረፍ እንዲያስችል ሪፖርት ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን አፅንኦት ሰጥተውበታል።

ፕሬዝዳንቱ አክለውም፤ አደጋ የደረሰባቸው ሰዎችን የተጠናቀረ መረጃ ለማግኘትና አጠቃላይ በግንባታ ሥራ የሚፈጠር አደጋን መቀነስ ላይ በቀጣይ ትኩረት ተደርጎ በስፋት እንደሚሰራበት አስታውቀዋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ