መስከረም 20/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) ባሳለፍነው የ2017 በጀት ዓመት ብቻ ከ18 እስከ 69 የእድሜ ክልል ውስጥ ባሉ ሰዎች ላይ በተደረገ የደም ግፊት ምርመራ 20 ነጥብ 5 በመቶ የሚሆኑት በምርመራ የተረጋገጠ ከፍተኛ ደም ግፊት እንደተገኘባቸው ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።
በዚሁ ጥናት መሠረት ከዚህ ቀደም በምርመራ የተረጋገጠ የከፍተኛ ደም ግፊት ካላቸው አዋቂዎች ውስጥ 60 በመቶ የሚሆኑት፤ የከፍተኛ ደም ግፊት የመድኃኒት ሕክምና እንደማያገኙ መረጃው ያመለክታል ተብሏል፡፡
የኢፌዴሪ ጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ደኤታ ደረጀ ድጉማ (ዶ/ር) ለአሐዱ እንደገለጹት፤ የከፍተኛ ደም ግፊት የምርመራ አገልግሎት ሽፋን 2008 ዓ.ም ከነበረው ቁጥር ለውጥ ያሳየ ሲሆን ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የተለያዩ ሥራዎችን ሲሰራ ቆይቷል።

በተለይም የቅድመ ልየታና ምርመራ ሥራዎችን ለማጠናከር የጤና ሚኒስቴር ለመሠረታዊ ጤና አገልግሎት መስጫ ጤና ተቋማት የሚሰራጩ ከ2 ሺሕ 900 በላይ ደረጃቸውን የጠበቁ የከፍተኛ ደም ግፊት መመርመሪያ ማሽኖች ገዝተው በበጀት ዓመቱ ለክልሎች መከፋፈላቸውን ገልጸዋል።
ጤና ሚኒስቴር የልብ በሽታን ከመከላከል አንፃር በምርመራ የተረጋገጠ የከፍተኛ ደም ግፊት ካላቸው ውስጥ 40 በመቶ የሚሆኑት የመድኃኒት ሕክምና እያገኙ መሆኑንና እንዲሁም፤ በቀጣይነት ቢያንስ ከሁለቱ የተረጋገጠ የከፍተኛ ደም ግፊት ካለባቸው ሰዎች ውስጥ አንዱን በመድኃኒት ለማከም እንደሚሰራ አስታውቋል።
በ2017 በጀት ዓመት የከፍተኛ ደም ግፊት ሕመም የስልጠና ማንዋሉ ላይ ያተኮረ ከ1 ሺሕ 800 በላይ ለሚሆኑ ሆስፒታሎችና ጤና ጣቢያዎች ስልጠና የተሰጠ ሲሆን፤ በዚህም የከፍተኛ ደም ግፊት ቅድመ ልየታ፣ ምርመራና ሕክምና አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኙ ተጠቁሟል።
በእንደ የዓለም ጤና ድርጅት ሪፖርት መሠረት በኢትዮጵያ የልብና ደም ግፊት በሽታዎች ዋነኛ የሞት መንስኤ ሲሆኑ፤ በተለይ የደም ግፊት ከ100 ሺሕ ሰዎች ውሰጥ 83 ነጥብ 7 ሰዎችን ሕይወት በመቅጠፍ ቀዳሚ እንደሆነ ተገልጿል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ