ሰኔ 26/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በዛሬው ዕለት የመንግሥትን የ2017 በጀት ዓመት የዕቅድ አፈፃፀም አስመልክቶ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት፤ "የሐኪሞች ጥያቄ ውድቅ የተደረገና ፖለቲካዊ ብቻ ነው አልተባለም" ብለዋል።

የምክር ቤት አባላት የሐኪሞቹን ጨምሮ አጠቃላይ የመንግሥት ሠራተኞችንና ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ዜጎችን የደመወዝ እና የኑሮ ደረጃ አስመልክቶ ጥያቄ አቅርበዋል።

የምክር ቤት አባሉ አበባው ደስአለው (ዶ/ር) የመንግሥት ሠራተኞችን ጨምሮ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የማኅብረተሰብ ክፍሎች የኑሮ ውድነቱን መቋቋም የማይችሉበት ደረጃ ላይ ስለመድረሳቸው አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።

Post image

የሕክምና ባለሙያዎችም ይህንኑ መሠረታዊ ጥያቄ በማንሳት፤ የጥያቄው ምላሽ በመዘግየቱ የሥራ ማቆም አድማ ማድረጋቸውን አስታውሰው፤ "ጥያቄያቸው የፖለቲካ ሥም ተሰጥቶት ሳይፈታ ተዳፍኖ ቀርቷል" ብለዋል።

ሌላኛው የፓርላማ አባል ግዛቸው አየለ በበኩላቸው፤ በተለያዩ ዘርፎች የተሰማሩ የመንግሥት ሠራተኞች የደመወዝ ማሻሻያ እንዲደረግላቸው እየጠየቁ እንደሚገኝ አንስተው፤ የኑሮ ደረጃቸውን ከማሻሻል አኳያ መንግሥት ማብራሪያ እንዲሰጥበት ጠይቀዋል።

Post image

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከፓርላማ አባላት ለተነሳላቸው የሐኪሞችን ጥያቄ የተመለከተ ጥያቄ በሰጡት ምላሽ "ሀኪሞች ጥያቄ ውድቅ የተደረገና ፖለቲካ ብቻ ነው አልተባለም። ያነሱት በጣም ተገቢ ጥያቄ ነው" ብለዋል።

ማብራሪያቸውን ሲቀጥሉም፤ "የእነርሱን ተገቢ ጥያቄ ለመሳፈር የሞከሩ ሰዎች ነበሩ። እውነተኛ ጥያቄ ቢሆንም ትክክል ባልሆነ መንገድ የቀረቡት ተለይተው ተቀምጠዋል" ሲሉ አንስተዋል።

"ሐኪሞቹ ምንም ምላሽ ያላገኙ አይመስለኝም፤ ተወያይተንና ተስማምተን፣ መምህራኖቹም ሆነ የጤና ባለሙያዎች የተግባባነው ነገር እኔና እናንተ የኢትዮጵያን ብልፅግና ለማረጋገጥ መስዋዕትነት ከፍሎ ልጆቻችንን ከድህነት ለመገላገል ስለሆነ መከራውን እንቀበልና ኢትዮጵያን እናሸጋግር ተባብለን ተግባብተን ተለያይተናል" ብለዋል።

የኑሮ ውድነትን በተመለከተው ምላሻቸው፤ "የዋጋ ግሽበት ለእድገት አስፈላጊ እንደሆነ አንስተዋል። የሸማቹ ገቢ በግሽበት መጠኑ ልክ አለማደጉ ግሽበቱን ጤናማ አያደርገውም ስለዚህ የዋጋ ግሽበትን ከፍላጎት ጋር ማጣጣም የሚቻለው እያንዳንዱ ግለሰብ ለፍላጎቱ የሚመጥን ገቢ ሲኖረው ነው" ብለዋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ