ሰኔ 26/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) መድኃኒት በዱቤ ወስደው ክፍያ የማይፈፅሙ እና ከስድስት ወር በላይ የሆናቸው ጤና ተቋማትን ተጠያቂ እንዲሆኑ የሚያስችል አሰራት መዘርጋቱ የመድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት አስታውቋል፡፡

የአገልግሎቱ የሕዝብ ግንኙነት ባለሞያ አቶ አወል ሀሰን፤ አገልግሎቱ በድጋፍ የሚገኙ መድኃኒቶችን በነጻ መደበኛ የሚባሉ መድኃኒቶችን ደግሞ በብድር እንደሚያቀርብ የገለጹ ሲሆን፤ መድኃኒት በብድር የወሰዱ ተቋማት በተገቢው መንገድ እየከፈሉ አለመሆኑን አስረድተዋል፡፡

በዚህም መሠረት መድኃኒት በዱቤ አገልግሎት ወስደው ክፍያ የማይፈጽሙ ጤና ተቋማት በ6 ወር ውስጥ ክፍያ ካልፈጸሙ በግዳጅ ከአካውንታቸው ገንዘቡን ለአገልግሎቱ እንዲሰጥ የሚያስችል የባንክ አሰራር መዝጋቱን ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡

የመድኃኒት ከፍተኛ ፍላጎት እና ዝቅተኛ አቅርቦት መኖር ተመጣጣኝ እንዳይሆን ማድረጉን የገለጹት የአገልግሎቱ የሕዝብ ግንኙነት ባለሞያው፤ ለጤና ተቋማት የመድኃት ፍላጎቱን ለማሟላት በቂ የሆነ በጀት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ መድኃኒት አገልግሎት ለትርፍ የተቋቋመ ድርጅት ባለመሆኑ፤ የመድኃኒት አቅርቦት ተደራሽ ለማድረግ በጀት ከፍተኛውን ድርሻ እንደሚይዝ እና የበጀት እጥረት ሲያጋጥም በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ተጽዕኖ እንደሚፈጠር ተናግረዋል፡፡

ችግሩን ለመፍታት በትብብር መስራት እንደሚገባ ያነሱም ሲሆን፤ "የጤና ተቋማት በቂ የሆነ በጀት ሊኖራቸው ይገባል" ብለዋል፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ