ሰኔ 26/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ‎በማይናማር በ3 ካምፓኒ ውስጥ 42 ኢትዮጵያውያን ታግተው የአካል ጉዳት እየደሰባቸው እና የሰብዓዊ መብት ጥሰት እየተፈጸመባቸው መሆኑን የታጋች ወላጆች ኮሚቴ ለአሐዱ አስታውቋል፡፡

"ልጆቻችን ከኢትዮጵያ ሲወጡ ሕጋዊ በሆነ በጎብኚዎች ፓስፖርት ሲሆን፤ የኮምፒውተር ሥራ አለ ተብለው ነው" ያሉት የኮሚቴው አባላት፤ ማይናማር ከደረሱ በኋላ የተባሉትን ሥራ አለማግኘታቸውን ተናግረዋል፡፡

"በአጋቾቹ አማካኝነት ከፍተኛ የሆነ የማጭበርበር ሥራ እንዲሰሩ ከመደረጋቸው ባሻገር፤ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እየተፈፀመባቸው ነው" ሲሉም ገልጸዋል።

‎ታጋቾቹ በተለያ የትምህርት ዘርፎች በድግሪና ከዛ በላይ ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ ሲሆን፤ ከ42 ታጋቾች መካከል 7ቱ ሴቶች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

የሚደርስባቸው ስቃይ እና ድብደባ ከፍተኛ መሆኑን ያነሱት የወላጅ ኮሚቴዎች፤ ምግብ እንደማያገኙ እና ለሞት እና ለአካል ጉዳት እየተዳረጉ መሆኑንም አንስተዋል፡፡

‎"የተሰጣቸው የጊዜ ገደብ አጭር በመሆኑ የኢትዮጵያ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ትልቅ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል" ሲሉም አሳስበዋል፡፡

Post image

ከዚህ በፊት ኮሚቴው በተደጋጋሚ ባቀረበው ጥያቄ መሠረት በኢትዮጵያ መንግሥተ ከፍተኛ ጥረት በመጠለያ ካምፕ የነበሩ ከ700 በላይ የሚሆኑ ዜጎች ከማይናማር ወደ ኢትዮጵያ መመለስ እንደተቻለ ለአሐዱ የገለጹም ሲሆን፤ "አሁን ላይ ቀሪዎቹ ልጆቻችን ወደሀገር እንዲመለሱ ለኢትዮጵያ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ተደጋጋሚ ጥያቄ ብናቀርብም ምላሽ ማግኘት አልቻልንም" ብለዋል፡፡

‎"መንግሥት ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት የልጆቻችንን ሕይወት እንዲታደግልን" ሲሉም ጠይቀዋል፡፡

‎ታጋቾቹ ከማይናማር ለአሐዱ በላኩት "የድምጽ የድረሱልን ጥሪ" ከባድ ሁኔታ ውስጥ መሆናቸውን የገለጹ ሲሆን፤ በአጋቾቹ ከሚደርስባቸው ከፍተኛ ድብደባ በተጨማሪ ለርሃብ እና እንደ ወባ ላሉ ሕመሞች እየተጋለጡ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

‎የኢትዮጵያ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ከዚህ ቀደም በሰጠው መግለጫ "ከ700 በላይ የሚሆኑ ዜጎችን መመለስ መቻሉን በመግለፅ፤ ነገር ግን አሁንም በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንን ለመመለስ እየተሰራ ነው" ማለቱ ይታወሳል፡፡

‎"መንግሥት በችግር ውስጥ ያሉ ኢትዮጵያውያንን ለመመለስ እየሰራ ቢሆንም ዜጎችን በሕገ-ወጥ መንገድ ወደ ውጪ ሀገር የሚልኩ ተቋማት እና ግለሰቦች እየጨመሩ መምጣታቸው የሚያሳዝን ነው" ያሉት የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ቃል ቀባይ አምባሳደር ነቢያት ጌታቸው፤ ሕብረተሰቡ ራሱንና ልጆቹን ሕጋዊ የውጪ ሀገር የሥራ ስምሪት ወዳልተፈረመባቸው ሀገራት እንዳይሄዱ ጥንቃቄ በማድረግ መከላከል እንዳለበት አሳስበዋል።

በማይናማር በአጋቾች ቡድን እጅ ከሚገኙ 42 ኢትዮጵያውያን መካከል አንድ ሰው ራሱን ሲያጠፋ፤ 1 ሰው ደግሞ በድብደባ ምክንያት ዐይኑን ማጣቱ አሐዱ ከዚህ ቀደም መዘገቡ ይታወሳል፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ