መስከረም 21/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) የልብ ሕክምና አገልግሎት ለማገኘት ረጅም ጊዜያት የሚጠብቁ ታካሚዎችን ችግር ለማቅለል ባሉበት ሆነው እንዲመዘገቡ እና ወረፋቸው ሲደርስ መጥተው መታከም እንዲችሉ የሚያስችል ሥራ በቅርቡ ተግባራዊ እንደሚደረግ የኢትዮጵያ የልብ ሐኪሞች ማህበር ለአሐዱ አስታውቋል።
ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች ምክንያት የሞት ቁጥር መጨመሩን ተከትሎ፤ መከላከል ላይ ያተኮረ ሥራ መሰራት እንዳለበት የማህበሩ ፕሬዝዳንት ዶክተር እንዳለ ገብሬ ተናግረዋል።
ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን 80 በመቶ ሙሉ በሙሉ መከላከል ስለሚቻል ቀደሞ መከላከል ላይ በትኩረት መሰራት እንዳለበት የገለጹት የማህበሩ ፕሬዝዳንት፤ በኢትዮጵያ ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች በተለይም የልብ ሕመም ሕክምና ለመስጠት በቂ የሕክምና መሳሪያ፣ የሰው ኃይል እና የመድኃኒት አቅርቦት አለመኖሩን ገልጸዋል።
በቅርቡ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ላይ በተለይም ከፍተኛ የደም ግፊት ባለባቸው ሰዎች ላይ የተሰራ ጥናት 16 በመቶ የነበረው ወደ 17 በመቶ ከፍ ማለቱን ዶክተር እንዳለ አክለዋል።
በዚህም 26 ሚሊዮን ሰዎች የደም ግፊት ምርመራ አድርገው ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ከፍተኛ የደም ግፊት ተገኝቶባቸዋል ብለዋል።
የቀድሞው የልብ ሐኪሞች ማህበር ፕሬዝዳንትና የልብ ሐኪም ዶክተር ከፈለኝ በበኩላቸው፤ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች መካከል የልብ ሕመምና ደም ግፊት ተጠቃሽ ሲሆኑ ኢትዮጵያን ጨምሮ በማደግ ላይ ያሉ ሀገሮች ሕክምናውን ለመስጠት የባለሙያና የሕክምና መሳሪያ እጥረት በመኖሩ መከላከል ላይ ያተኮረ ሥራ መሰራት እንዳለበት ጠቁመዋል።
አክለውም ከዚህ ቀደም በምርመራ የተረጋገጠ የከፍተኛ ደም ግፊት ካላቸው ሰዎች ውስጥ 60 በመቶ የሚሆኑት የከፍተኛ ደም ግፊት የመድኃኒት ሕክምና እንደማያገኑ መረጃው እንደሚያመላክት ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡
ማህበሩ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር እየሰራ መሆኑ ሲሆን፤ ሕብረተሰቡ የአኗኗር ዘይቤውን በማስተካከል ተላላፊ ካልሆኑ በሽታዎች ራሱን መጠበቅ እንዳለበት ማሳሰቢያ ተላልፏል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
የልብ ሕክምና አገልግሎት ለማገኘት ከተለያዩ አካባቢዎች ወደ መዲናዋ የሚመጡ ሕሙማን ባሉበት ሆነው እንዲመዘገቡ የሚያስችል ሥራ በቅረቡ ተግባራዊ ይደረጋል ተባለ
