መስከረም 21/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ባለፉት አምስት ዓመታት ስትተገብረው የነበረውን ብሔራዊ የጤና ደህንነት ትግበራ አጠናቃ ወደ ሁለተኛው መሸጋገሯን ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር መቅደስ ዳባ እንደገለጹት ብሔራዊ የጤና ደህንነት ትግበራ በኢትዮጵያ እስከ ወረዳዎች እና ቀበሌያት ድረስ የሚሰራ ሲሆን፤ የጤና ተቋማትን ማሻሻል፣ የጤና ተደራሽነትን ማስፋት እና በሰዎች ብቻ ሳይሆን በሁሉም የጤና ዘርፎች ላይ መሻሻሎች እንዲመጡ በቅንጅት የሚሰራበት ነው፡፡
ለዚህ ደግሞ እስከዛሬ የነበሩ ስህተቶችን በማረም እና ከመጀመሪያው ትግበራ የታዩ ጉድለቶችን በመሙላት የሁለተኛውን መርሃ ግብር አስጀምረናል ሲሉ ነው ሚኒስትሯ የገለጹት፡፡
መርሀ ግብሩ ከዚህ በፊት የተሰሩ ሥራዎችን ገምግሞ ለቀጣይ አምስት ዓመታት በጤናው ዘርፍ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት ታልሞ የተዘጋጀ ሲሆን፤ ስትራቴጅክ እቅዱ ከአውሮፓውኑ 2025 እስከ 2030 የሚተገበር ነው ብለዋል።
በዚህኛው መርሃ ግብር ላይ በሰዎች ጤና ላይ ብቻ ሳይሆን በሰዎች ጤና ላይ ተፅእኖ ሊያሳድሩ የሚችሉ የእንስሳት ጤና የተክሎች ጤና እና የሌሎችም ከሰዎች ጋር ንክኪ ኖሯቸው የጤናው ዘርፍ ላይ ተፅዕኖ ሊያመጡ የሚችሉ ዘርፎች ላይ ከባለድርሻ አካላት ማለትም ከግብርና ሚኒስቴር፣ ከትምህርት ሚኒስቴር፣ ከዱር እንስሳት ጥበቃ ባለስልጣን፣ ከአከባቢ ጥበቃ ባለስልጣን እና ከሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትት ጋር በመሆን የሚሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የተጠቀሱት ተቋማት በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ከጤና ጋር የሚገናኙ ሥራዎች ላይ የሚያተኩሩ በመሆናቸው፤ ሁሉም አንድ ሆኖ የአንድ ጤና ስልታዊ ትግበራ ላይ የሚሳተፍ ይሆናል ሲሉም ለአሐዱ ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ የዓለም ጤና ደንብ (አይ.ኤች.አር) አባል እና ፈራሚ ሀገር ስትሆን እንደ አዉሮፓውያን የዘመን ቀመር ሰኔ 15 ቀን 2017 ጀምሮ ሁሉም አባል ሀገራት ዓለም አቀፍ የጤና ደህንነት ዋና አቅሞችን ማለትም የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች የመከላከል እና ሊደርሱ የሚችሉ ማህበራዊ ኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖዎችን በተሳካ ሁኔታ መከላከል፣ መቀነስ፣ ማጥፋት እና ሲከሰትም ምላሽ መስጠት የሚያስችል አቅም መገንባት አስገዳጅ እንዲሆን በመወሰኑ ኢትዮጵያ እነኝህን ተግባራት አከናውናለች ነው የተባለው፡፡
ሁለተኛው የብሔራዊ ጤና ደህንነት ትግበራ 19 ትኩረት የሚሰጣቸው ጉዳዮች በዋናነት የተያዙበት መሆኑ ተገልጿል፡፡
በመርሀ ግብሩ ላይ የዓለም ጤና ድርጅት ተወካይ ፕሮፌሰር ፍራንሲስ ካሶሎ ባደረጉት ንግግር፤ የጤና ደህንነት ጉዳይ ምርጫ ሳይሆን ከሌሎቹ ጉዳዮች በላይ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ነው ብለዋል፡፡
ይህ የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ እቅድ ለጤናው ዘርፍ የተሰጠውን ትኩረት ያሳያል ያሉት ፕሮፌሰሩ፤ የእቅዱን ጥሩነት ለመለካት ከሀሳብ ወደ ተግባር፣ ከተግባር ወደ ውጤት መቀየር ያስፈልጋል ሲሉ አጽንዖት ሰጥተውበታል።
የዓለም ጤና ድርጅትም በዚህ ጉዳይ ላይ ድጋፋን እንደሚቀጥል አክለው ተናግረዋል።
በዚህ የጤና ደህንነት መርሃ ግብር ማስጀመሪያ ላይ የዓለም ጤና ድርጅት እና የዓለም እርሻና ምግብ ድርጅት ተወካዮችን ጨምሮ፤ የጤናና የግብርና ሚንስትሮች እንዲሁም ሌሎችም ባለድርሻ ተቋማት ተወካዮችና ከፍተኛ ባለሥልጣናት ተገኝተዋል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
ሁለተኛው የብሔራዊ ጤና ደህንነት ትግበራ በመጀመሪያው ትግበራ የታዩ ስህተቶችን በማረም ይተገበራል ተባለ
የዓለም ጤና ድርጅት ለጤና ዘርፉ የሚሰጠው ትኩረት ምርጫ ሳይሆን ግዴታ መሆኑን ገልጿል
