ሰኔ 26/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ዘንድሮ ለኢትዮጵያ በእጅጉን የማንሰራራት ዘመን ነው፡፡ ታላላቅ ድሎች የተመዘገቡበት፣ አመርቂ ውጤቶች የታዩበት በኢትዮጵያ ታሪክ ታይተው ያልታወቁ ድሎች የተጎናጸፍንበት ዓመት ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ተናግረዋል፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 42ኛ መደበኛ ስብሰባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በተገኙበት በመካሄድ ላይ ይገኛል፡፡

የምክር ቤት አባላቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የተለያዩ ጥያቄዎችን ያነሱ ሲሆን፤ በአሁኑ ሰዓት ጠ/ሚኒስትሩ ከአባላቱ ለተነሱላቸው ጥናያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ እየሰጡ ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በምላሽቸው በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ የኢትዮጵያ ማንሰራራት ዓመት ጅማሮ እንደሚሆን መግለጻቸውን አስታውሰው፤ "ማንሰራራት ብለን ያነሳነው ሃሳብ የለውጥ መትከል የለውጥ ማጽናት የለውጥ መሰረት ማስያዙ ምዕራፍ ተጠናቆ ወደ እድገት የሪፎርሙን ውጤት ሃርቨስት ወደምናደርግበት ጊዜ መሸጋገራችንን ለመግለጽ ነበር ያንን ቋንቋ መጠቀም ያስፈልገው፡፡" ብለዋል፡፡

"በመሆኑም ዘንድሮ ለኢትዮጵያ በእጅጉን የማንሰራራት ዘመን ነው" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ "ይህ ጉዳይ እንዲሳካ የተከበረው ምክር ቤት እጅግ ከፍተኛ አስተዋጽዖ ስላደረገ ምክር ቤቱን እና ሰፊውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ለተገኘው ድል ለነበራችሁ አስተዋጽዖ በራሴ እና በኢፌዲሪ መንግስት ሥም እንዳመሰግን ይፈቀድልኝ" ብለዋል፡፡

Post image

አክለውም የምክር ቤቱ አባላት ቁጥጥር ብቻ ሳይሆን ክትትል እና ድጋፍ በማድረግ በእያንዳንዱ ሥራ ውስጥ የሰጡት አመራር ለተገኘው ውጤት ከፍተኛ ድርሻ እንዳለው ገልጸው፤ ይህ ልማድ በሚቀጥሉት ዓመታት ተጠናክረው እንዲቀጥሉ አሳስበዋል፡፡

በማስከተልም የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም በሚመለከት መረጃዎችን ያጋሩት ጠ/ሚኒስትሩ፤ "የማክሮ ኢኮኖሚ ፎርም የጀመርነው አጠቃላይ የመንግሥታችን መርህ በአቢዮት ሳይሆን በሪፎርም ፖለቲካው ኢኮኖሚያውን ማህበራዊ ዘርፉን ተቋማትን መለወጥ ይቻላል በሚል ነው" ብለዋል፡፡

"የነበረውን ሳናፈርስ በነበረው ላይ የጎደለ እየሞላ እያዘምን የተሻለች ታሪኳን ያዘነጋች ወደፊት ያላት ተስፋ የሚታይ ኢትዮጵያን መስራት ይቻላል ከሚል የመነጨ ነው" ሲሉም ገልጸዋል፡፡

"ኢኮኖሚን በሚመለከት ወደ ማክሮ ሪፎርም እንድገባ ያስገደድን ጉዳዮች አንደኛው የማክሮ ኢኮኖሚ ስብራቶች ናቸው" ያሉት ጠ/ሚኒስትሩ፤ እነዚህ ስብራቶች በሥራ አጥነት፣ በኑሮ ውድነት፣ በገቢና ውጭ ወጪ ንግድ ሊገለጹ እንደሚችሉ አንስተዋል፡፡

"ሁለተኛው ወደ ሪፎርም ያስገባል የግል ዘርፍ መነቃቃት እንዲችል የሥራ አካባቢው ምቹ አልነበረም" ያሉ ሲሆን፤ እንደ ማሳያ ለማቅረብ የግሉ ዘርፍ በተለያዩ ባንኮች የሚያስቀምጣቸው ገንዘቦች 27 በመቶው ቦንድ በሚል ስለሚወሰድ በቂ ሃብት ፈሶለት ሥራ ለመስራት የሚያስችል እድል አልነበረም" ብለዋል፡፡

"ሦስተኛው ምርታማነት ነው" ያሉ ሲሆን፤ "በግብርናም በኢንደስትሪውም ምርታማ የመሆን ውስንነት ነበር፡፡ ምርታማ ባለመሆናችን ደግሞ ሲነሱ የነበሩ በርካታ ችግሮች አገራችን ውስጥ እንዲስተናገዱ ሆኗል፡፡" ሲሉ ገልጸዋል፡፡

አራተኛው ተወዳድሮ የሚያሸንፍ የኢኮኖሚ ሁኔታን መፍጠር አልቻልንም የሚል መሆኑን አንስተው፤ "እነዚህን ጉዳዮች ጨክነን በመፍታት ኢትዮጵያ ውስጥ ያለ የማክሮ ስብራት ደረጃ በደረጃ ሊቀረፍ ይችላል። የሚል እምነት ተይዞ ነው ሥራው የተጀምረው" ብለዋል፡፡

"ይህ ሥራ ውስጥ ተጀምሮ ኢትዮጵያ ውስጥ ተጀምሮ ኢትዮጵያ ውስጥ አያልቅም" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፤ "ከዓለም ጋር ባለን ትስስር ምክንያት አንዳንድ ፍላጎታችን የዓለምን የኢኮኖሚ ሂደት እና ጉዞ የማንገነዘብ የማናይ የማናነብ ከሆነ የኛ ፍላጎት ብቻውን በበቂ ደረጃ ሊሳካ አይችልም" ሲሉ አስረድተዋል፡፡

ከዚህ አንፃር አለም ላይ የነበረው አጠቃላይ የኢኮኖሚ ሂደት ከፍተኛ መዋዠቅ የታየበት እንደነበር አንስተው፤ እንደ አይኤምኤፍ ትንበያ መሠረት ዘንድሮ አጠቃላይ የዓለም ዕድገት 3 ነጥብ 3 በመቶ ሊሆን እንደሚችል አስቀድሞ ተንብዮ የነበረ እንደነበር አንስተዋል፡፡

"ነገር ግን በሂደት ዓመቱ እየተጋመሰ ሲሄድ ካጋጠሙ አዳዲስ ችግሮች በመነሳት፤ የዓለም እድገት ከትምበያው ዝቅ ብሎ 2 ነጥብ 8 ገደማ ሊሆን እንደሚችል አስቀምጧል" ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል አይኤምኤፍ እና የዓለም ባንክ የኢትዮጵያ ሪፎርም ችግር ያለበት ነዉ በሚል ሪፖርት አቅርበዋል በሚል ብዙ ሲተች መቆየቱን አንስተዋል፡፡

አክለውም፤ ነገር ግን ሪፎርሙ በዓለም አቀፍ የፋይናንሻል ኮሚቴ ጭምር የተመሰገነ እና ብዙዎች ምሳሌ ሊያደርጉት የሚችሉት ሪፎርም መሆኑን የአይኤምኤፍ ሪፖርት እንደሚያሳይ ተናግረዋል፡፡

ከሪፎርሙ በኋላ በኤክስፖርት ለማግኘት ካቀድነዉ 5 ነጥብ 1 ቢሊየን ዶላር ዕቅድ አሁን ላይ 8 ነጥን 1 ቢሊየን ዶላር ማግኘት ችለናል ያሉም ሲሆን፤ "ዕቅድ አሳክታ የማታዉቅ አገር ካቀደችዉ በላይ አሳክታለች" ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለፈው ዓመት 8 ነጥብ 1 በመቶ ዕድገት ተመዝግቦ እንደነበር ያስታወሱም ሲሆን፤ እስከ መስከረም በሚኖረዉ ጊዜ 8 ነጥብ 4 በመቶ እና ከዛ በላይ ዕድገት እንደሚመዘገብ አስታውቀዋል፡፡

አክለውም "አምርታ መብላት የማትችል አገር ብሔራዊ ጥቅሞቿን ለማሳካት ትቸገራለች" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ "ኢትዮጵያ የምግብ ሉዓላዊነቷን ማረጋገጥ አለባት" ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ባለፉት ጥቂት ዓመታት 27 ሚሊየን ገደማ ሰዎች በሴፍቲኔት የታቀፉ ተረጂዎች እንደነበሩ የገለጹ ሲሆን፤ አሁን ላይ 23 ሚሊየን ኢትዮጵያውያን እራሳቸው አምርተው ከሴፍቲኔት ተረጂነት ወጥተዋል ብለዋል

"ኢትዮጵያ ሊታረስ የሚችል በጣም ሰፊ መሬት ካላቸው ሀገራት አንዷ ነች" ያሉም ሲሆን፤ "ባለፈው ዓመት ብዙ ጨምረናል ብለን 26 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ታርሶ ነበር በዚህኛው ዓመት ግን 31 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ማረስ ተችሏል፡፡ 5 ነጥብ 8 ሚሊየን ሄክታር ተጨማሪ ቦታ አርሰናል" ሲሉ አስረድተዋል፡፡

Post image

ባለፈው ዓመት በጥቅሉ ከሁሉም ዓይነት የሰብል ምርቶች 1 ነጥብ 2 ቢልየን ኩንታል ምርት መሰብሰቡን በማንሳትም፤ ዘንድሮ ግን 300 ኩንታል ጨምሮ 1 ነጥብ 5 ቢሊየን ኩንታል መሰብሰብ መቻሉን ተናግረዋል፡፡

"ይህ እድገት የመጣው አንደኛ በመስኖ ሥራ ነው" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፤ "የመስኖ ሥራን አስመልክቶ በከፍተኛ እና በተወሰኑ መካከለኛ ፕሮጀክቶች በፌደራል መንግሥት 20 ገደማ ግድቦች ይሰራሉ" ሲሉ አስታውቀዋል፡፡

"እነዚህ ግድቦች ሲጠናቀቁ ከ220 ሺሕ በላይ ሄክታር በላይ መሬት በዓመት ማልማት ይችላሉ፡፡ በዓመት ሁለቴ ከታረሱ 440 ሺሕ ሦስተኛም ከታረሱ 6 ሺሕ 600 ገደማ ሄክታር ይሆናል" ሲሉ አስረድተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም፤ በዚህ ዓመት እስከ መስከረም ባለው ጊዜ ውስጥ ቢያንስ 84 ሄክታር መሬት ማልማት የሚችሉ ቢያንስ 6 ከፍተኛ ግድቦች እንደሚመረቁ አስታውቀዋል፡፡

በዚህም "ኢትዮጵያ መለመን ያለባት ልጆቿ ተግተው ሰርተው ከልመና እራሳቸውን መገላገል አለባቸው የሚለው እምነት ፍሬ እያፈራ ነው" ብለዋል፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ