ጥቅምት 12/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) መንግሥት ተፎካካሪ የፓለቲካ ፓርቲዎች የሚያቀርቡትን የሰላም ጥሪ ለመቀበል ፈቃደኛ አይደለም ሲሉ አንድ ኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ፓርቲ እና የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) ገልጸዋል፡፡
በሀገሪቱ የሚገኙ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ለሚስተዋሉ የፀጥታ ችግሮች እንዲፈቱ የሰላም ጥሪ ሲያቀርቡ ብሎም ውይይት የሚደረግባቸው መንገዶች ለመቀየስ ሲሞክሩ ይስተዋላል።
አሐዱ "የፓለቲካ ፓርቲዎች የሚጀምሯቸው የሰላም አማራጮችና ጥሪዎች ስለምን ምላሽ አላገኙም?" "ውጤታማነታቸውስ እንዴት ይታያል?" ሲል ፓርቲዎችን ጠይቋል።
የፓለቲካ ፓርቲዎቹ በምላሻቸው የምናደርጋቸው የሰላም ጥሪዎች መንግሥት በበጎ ለመመልከት ፈቃደኛ ባለመሆኑ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) የፋይናንስና ንብረት አስተዳደር ሥራ አስፈጻሚ ሙሉጌታ ሀድጉ፤ በፓርቲ ደረጃ የቀረበ ሀሳብ ቀርቶ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተደረሱ ስምምነቶች እየፈረሱ መሆኑን ለማሳያነት አቅርበዋል።
ስለሆነም በመንግሥት በኩል "ተፎካካሪዎች የሰጡት ሀሳብ ምን ይጠቅመኛል" በሚል ሀሳባቸውን የመቀበል ፍላጎት የለም ሲሉ ገልጸዋል።
እንዲሁም ተፎካካሪ ፓርቲዎች ያላቸው አቅም ውስን ነው ያሉ ሲሆን፤ የተለያዩ አማራጮችን በመጠቀም ለሰላም ውትወታ ማድረግ ዋነኛው ሚናቸው መሆኑን ከግምት ማስገባት አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል።
"በመንግሥት በሚመራ ሀገር ውስጥ ሰላም ለማምጣት መንገዶችን ማመቻቸው የመንግሥት ሚና ነው" የሚሉት ደግሞ፤ የአንድ ኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ፓርቲ ሊቀመንበር ሲሳይ ደጉ ናቸው።
"እንደ ፓርቲ መንግሥት ሊያደርጋቸው የሚገቡ ኃላፊነቶችን እንገልጻለን" ያሉት ሊቀመንበሩ፤ መንግሥትን የመሞገት ተግባራትን ሲከውን ቆይቷል ብለዋል። ነገር ግን የፓርቲዎችን ሀሳብ ተጋርቶ የሚሄድ ፍላጎት ከመንግሥት በኩል አለመኖሩን ገልጸዋል።
አክለውም የፓለቲካ ፓርቲዎች የሚያቀርቧቸው ጥያቄዎች በተቃራኒው መልሰው ተጠያቂነትን የሚፈጥሩ ናቸው ብለዋል።
ስለሆነም መንግሥት ከተፎካካሪ የፓለቲካ ፓርቲዎች ጋር በጋራ መስራት፣ መግባባት የሚያስችለውን መንገድ መፍጠር አለበት ሲሉ የፓለቲካ ፓርቲዎቹ ገልጸዋል።
እንዲሁም የሚሰጡ ሀሳቦች ለሀገር ጥቅም እንጂ ሆነ ተብሎ መንግሥትን የማሳጣት አላማን ያነገቡ አለመሆኑ ልብ ሊባል ይገባል ብለዋል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
መንግሥት ተፎካካሪ የፓለቲካ ፓርቲዎች የሚያቀርቡትን የሰላም ጥሪ ለመቀበል ፈቃደኛ አይደለም ተባለ
