ጥቅምት 18/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) በአማራ፣ ኦሮሚያ እና በሌሎች አካባቢዎች ያሉ ጦርነትና ግጭቶች ጉዳት የደረሰባቸው ሰላማዊ ሰዎች እና መሠረተ ልማቶች ጉዳት ይፋ እንዲደረግ የምክር ቤት አባሉ ደሳለኝ ጫኔ (ዶ/ር) ጠይቀዋል፡፡

6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 2ኛ መደበኛ ስብሰባ ዛሬ ጥቅምት 18 ቀን 2018 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በተገኙበት በመካሄድ ላይ ይገኛል፡፡

በመደበኛ ስብሰባው ላይ የምክርቤቱ አባላት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የተለያዩ ጥያቄዎችን ያነሱ ሲሆን፤

👉የኑሮ ውድነትን በዘላቂነት ለመፍታት እና ህገ ወጥ የዋጋ ንረት ለመከላከል በመንግሥት በኩል የተወሰደ እርምጃ እና ቀጣይ አቅጣጫ ምን ይመስላል?፣

👉 የፕሪቶሪያውን ስምምነት ወደ ጎን በመተው የኢትዮጵያን ሕዝብ ዳግም ወደ ጦርነት ለማስገባት እየተስራ ያለውን ሂደት አደብ ለማስገዛት ምን እየተሰራ ነው? የአሁናዊ የትግራይ የሰላምና የፀጥታ ሁኔታስ እንዴት ይታያል?

👉7ኛው ሀገራዊ ምርጫ በተለመደው ሁኔታ ነው የሚካሄደው ወይስ ከሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የሚሰጡ ምክር ሀሳቦችን አካቶ ነው ይህ ከሆነ ጊዜ አያጥርም ወይ ቢብራራ?

👉 የባህር በር ጥያቄን ከጎረቤት ሀገር ኤርትራ ጋር እንዴት ይታያል፤ የአለም አቀፍ ማህበረሰቡም ይህ ጉዳይ ሰላማዊ እና ህልውና ጥያቄ እንደሆነ እንዲገነዘቡ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች ቢገለጹ፤

👉 የቤት ችግርን ለመፍታት እና የቤት አቅርቦትን ለመጨመር እየተሰሩ ያሉ ስራዎችን በተመለከተ መንግስት ያስቀመጣቸው አቅጣጫዎች ለምክር ቤቱ ቢነሱ? የሚሉና ሌሎች ወቅታዊ፣ ሀገራዊና ፖለቲካዊ ጥያቄዎች ተነስተዋል፡፡

Post image


የምክር ቤት አባሉ ደሳለኝ ጫኔ (ዶ/ር) ለጠቅላ ሚኒስትሩ ባነሱት ጥያቄ አስቀድመው፤ "ዛሬም የማነሳቸው ጥያቄያዎችን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመጨለምተኛነት እንዳይወስዷቸው" ሲሉ ያሳሰቡ ሲሆን፤ “ጥያቄዎቹም የሕዝብ በመሆናቸው እንጂ ጨለምተኛ በመሆኔ አይደለም” ብለዋል።

"ግል ሕይወቴም ሆነ በፖለቲካ ልምዴ ተስፈኛ እንጅ ጨለምተኛ አይደለሁም" ያሉት ዶ/ር ደሳለኝ፤ "ጥያቄ ለእርስዎ ማናሳለዎት የሕዝብ ጥያቄዎች ተገቢ ትኩረትና ምላሽ እንዲያገኙ ስለሚገባ ነው" በማለት ወደ ጥያቂያቸው አልፈዋል፡፡

አክለውም፤ በአማራ፣ ኦሮሚያ እና በሌሎች አካባቢዎች ያሉ ጦርነትና ግጭቶች ተባብሰው በመቀጠላቸው ብዙዎች እየተጎዱ ነው፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩም እንደ ጸጥታ መሪነትዎ በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች በእነዚህ ጦርነቶች ምክንያት የተጎዱ ሰላማዊ ሰዎችና የሰላማዊ ሰዎች መሠረተ ልማቶች ቁጥር በግልጽ ይፋ እንዲያደርጉ እጠይቃለው" ብለዋል

"የጸጥታ ችግሮቹን ለመፍታት “ጽንፈኛ” እና “አሸባሪ” የሚላቸውን ቡድኖች ከመውጋት ባለፈ ለሁለቱ ክልሎች ከወታደራዊ አማራጮች ውጪ የተለየ ፖለቲካዊ መፍትሔ ለመስጠት መንግሥት ለምን አይሰራም” ሲሉም ጠይቀዋል፡፡

Post image

ስለሆነም "በኦሮሚያና በአማራ እንዲሁም በትግራ ካሉ ሀይሎች ጋር መንግስት ከሀይል ውጭ በሰላም እና በድርድር እንዲፈታ እጠይቃለው" ሲሉ አሳስበዋል፡፡

የምክር ቤት አባሉ አክለውም “የኢትዮጵያ ሕዝብ የእርስ በእርስ ጦርነት አንገፍግፎታል፣ በሀገር ውስጥ ተንቀሳቅሶ ሰርቶ መብላት ከብዶታል፤ ሀገራችንም እንደ ኮሎምቢያ ከውስጥ ታጣቂዎች ጋር ሀምሳ ዓመታትን እየተዋጋች ልትቀጥል አትችልም" ሲሉ ገልጸዋል

በተጨማሪም የፖለቲካ እስረኞች በተደጋጋሚ የፍርድ ቤት ቀጠሮ የለ ፍርድ እየተንገላቱ ነው። ቤተሰቦቻቸውም ከፍተኛ ችግር ውስጥ ናቸው። በሕግ የበላይነት ስም የሚፈፀሙ የዘፈቀደ እስሮች ቀጠዩን 7ኛ ሀገራዊ ምርጫ እንዳየበላሹ መንግስት ምን ዋስትና መስጠት ይችላል? ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

በተጨማሪም የዓለም ባንክ ሪፖርት ከሁለት ኢትዮጰያውያን አንዱ ደህነት ላይ እንደረፉ ይጠቁማል፤ መንግሥት ይሄን ለመቅረፍ ምን አቅድ አለው? ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

"የሀገር ውስጥ ሰላምና ኢኮኖሚ አጣዳፊ ጉዳይ ሆኖ ሳለ መንግሥት በውጭ ጉደይ ላይ ተጠምዷል። ብሔራዊ ጥቅምን ማስጠበቅን የሚደረግ ዲፕሎማሲያዊ ጥረትን በግሌ እቀበለዋለው" ያሉት ዶ/ር ደሳለኝ፤ "ነገር ግን መንግሥት ከሶማሌላንድ፣ ከጅቡቲ በወደብ ጉዳዮች ላይ የሞከረው ጥረት አልተሳካም። ከኤርትራም ጋር ያለው የቀይ ባህር ጥያቄ በጦርነት ሳይሆን በዲፕሎማሲ እና ሰጥቶ መቀበል ላይ መሆን አለበት" ሲሉ አሳስበዋል፡፡

አክለውም "መንግሥት የቀይ ባሕርን አደንጃ ያነሳበት መንገድ ስድስት ድስት ጥዶ አንዱን የማሳረር ሂደት ነው፡፡

በአሁኑ ወቅትም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ከምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ እና ማብራሪያ በመስጠት ላይ ይገኛሉ፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ