ጥቅምት 11/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ 7ተኛውን ሀገራዊ ምርጫ ለማከናውን የጊዜ ሰሌዳ ይፋ ማድረግና የተለያዩ ተግባራትን እንደሚያከናውን ይጠበቃል።
ይህም ሲሆን 7ተኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ ለፌደራል እና ለክልል ምክር ቤት መቀመጫዎች እንዲሁም፤ ለአዲስ አበባ እና ለድሬደዋ ከተማ መስተዳድር ምክር ቤቶች ምርጫ እንደሚካሄድ ተጠባቂ ነው።
አሐዱም ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ የህብር ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ እና የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) አነጋግሯል።
የሕብር ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ የሆኑት ምዕራፍ ይመር፤ የሕዝብን ድምጽ ለመግዛት ፖሊሲዎቻቸውን በይፋ የሚያስተዋውቁበት እና በቃላቸው መሠረት ሊጠየቁ የሚችሉባቸውን ጉዳዮች የሚያነሱበት ብሎም ቃል የሚገቡበት በቃላቸውም መነሻነት በጊዜ ሂደት የሚዳኙበት መድረክ በጊዜው ለመጠቀም ቅድም ዝግጅት ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
የአንድን ሀገራዊ ምርጫ ውጤት ከሚወስኑ አብይ ሒደቶች መካከል የምርጫ ቅስቀሳ ሂደት አንዱ ጉዳይ ነው ሲሉ ጠቁመዋል።
በዚህም መሰረት ፓርቲያቸው "በምረጡኝ ዘመቻው ወቅት ምን ዓይነት ርእሰ ጉዳዮችን ማንሳት ይገባዋል? የትኞቹ አጀንዳዎች ቅድሚያ ሊሰጣቸው ይገባል? ብለን የማየት ሥራዎች ስንሰራ ነበር ብለዋል።
በአንዳንድ አከባቢዎች ያሉ የጸጥታ ችግሮች በወቅቱ የምርጫ ቅስቀሳ ለማድረግ አስቻይ አለመሆኑን አንስተው፤ መሰል ችግሮችን መንግሥት የመቅረፍ ኃላፊነት እንዳለበት አብራርተዋል።
"እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ሀሳባቸውን አቀራርበው መሰባሰብ ያቃታቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች በበዙበት ሀገር፤ ሕዝቡ ፓርቲዎችን በግልጽ ለመዳኘት የሚችልባቸውን መድረኮች ማግኘት አስቸጋሪ ነው" ሲሉም ጠቁመዋል።
በአሁኑ ወቅት ያሉት ፓርቲዎች በርካታ መሆናቸውን ጠቁመው፤ ይህ መሆኑ ደግሞ መራጩን ሕዝብ ከማደናገር ባለፈ በትላልቅ ሀገራዊ ጉዳዮች ወይም አጀንዳዎች ላይ እንዳያተኩሩ ያደርጋል ሲሉ ገልጸዋል።
አሐዱ ያነጋገራቸው፤ የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ የሆኑት አቶ ይስሃቅ ወልዳይ በበኩላቸው፤ በወቅቱ የ'ይምረጡኝ' ቅስቀሳ ለማድረግ መዘጋጀታቸውን አብራርተዋል።
ነገር ግን አሁንም ቢሆን በሀገሪቱ ምርጫ ለማድረግ አስቻይ ሁኔታ የለም ያሉት ኃላፊው፤ አስቻይ ሁኔታን የመፍጠር ግንባር ቀደም ኃላፊነት የመንግሥት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በዚህም መንግሥት የታጠቁ ሃይሎች ወደ ድርድር የሚመጡበት ሁኔታዎችን ማመቻቸት እንዲሁም የዜጎች በሰላም ወጥቶ መግባት ማረጋገጥ ይገባዋል ሲሉ አሳስበዋል።
እነዚህን ቅድመ ሁኔታዎችን በሟሟላት ምርጫ ማድረግ ይገባል ነው ያሉም ሲሆን፤ ቅድመ ሁኔታዎች ሳይደረጉ ምርጫ መደረግ አለበት ብለው እንደማያምኑ አስረድተዋል።
በይፋ እንደሚጀመር የሚጠበቀው የምርጫ ቅስቀሳ ፓርቲዎች ከአባላት እና ደጋፊዎቻቸው ጋር በዛ ባለ ቁጥር የሚገናኙበት መሆኑን ይታወቃል።
ምርጫ ቅስቀሳ በምርጫ ሂደት ወሳኝ ከሚባሉ ሂደቶች አንዱ ነው፡፡ ስለሆነም ፓርቲዎች በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት በዋና ዋና ጉዳዮች ላይ መሠረታቸውን አድርገው፣ የምርጫ ሕጎችን በሚገባ ተገንዝበው ለራሳቸው ሕገ ደንብ ጭምር በመገዛት እንዲያከናውኑ ይጠበቃል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
የምርጫ ቅስቀሳን በወቅቱ ለማድረግ ቅድመ ዝግጅቶችን ማጠናቀቃቸውን የፖለቲካ ፓርቲዎች ገለጹ
አሁንም ግን በሀገሪቱ ምርጫ ለማድረግ አስቻይ ሁኔታ የለም ተብሏል
