ጥቅምት 18/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ መንግሥት አንድም ዶላር የንግድ ብድር አልወሰደም። ይህም እዳን ለመቆጣጠር ያለንን ጽኑ አቋም ያሳያል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ተናገሩ፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ምላሽና ማብራሪያ እንዲሰጡባቸው ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ ዲፕሎማሲያዊ እና የሰላምና ጸጥታ ጉዳዮችን የተመለከቱ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ያቀረቡ ሲሆን፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለጥያቄዎችና አስተያየቶች ምላሽና ማብራሪያ በመስጠት ላይ ይገኛሉ።

በማብራሪያቸውም ኢትዮጵያ አሁን ላይ እዳዋን ለመክፈል ምንም ችግር የለባትም። በሪፎርሙ አመካኝነት ከ4 አስከ 4 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር የሚደርስ የእዳ ሽግሽግ ተደርጓል። ይህም ኢትዮጵያ አሁን ላይ እዳዋን ለመክፈል ምንም ችግር እንደሌለባት አመላካች ጉዳይ ነው" ብለዋል፡፡

ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ መንግሥት አንድም ዶላር የንግድ ብድር አልወሰደም። ይህም እዳን ለመቆጣጠር ያለንን ጽኑ አቋም ያሳያል ሲሉም ገልጸዋል፡፡

አፍሪካ ውስጥ ከ1 እስከ 3ኛ ደረጃ ኢኮኖሚ ያላቸው ሀገራት ከኢትዮጵያ በብዙ እጥፍ የሚበልጥ እዳ አለባቸው፡፡

ኢትዮጰያ ያለባት ብድር ከ23 ቢሊየን ዶላር አይበልጥም ይህን እዳ በአጭር ጊዜ ብዙ ለመክፈል በሚቻልበት መንገድ ብድር ስለተወሰደ ከባድ የሚዲያርገው እሱ ነው ሲሉም አስረድተዋል፡፡

በዚህም የብድር ሁኔታው እንዲሸጋሸግ መንግስት ድርድር ሲያደርግ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ 2017 ዓ.ም በኢትዮጵያ ታሪክ ታላላቅ እና አይቻሉም የተባሉ ጉዳዮችን እውን ያደረግንበት የስኬት ዓመት ነበር ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም የሀገሪቱን ግብርና መር የኢኮኖሚ አካሄድ፤ ከአንድ ዘርፍ ወደ ብዝኃ ዘርፍ በመቀየር ተጨባጭ ለውጥ እየመጣ ነው ሲሉም ገልጸዋል

መንግሥት የኢትዮጵያን ልማት ለማፋጠንም ከግሉ ዘርፍ ጋር በጥምረት፤ ከሕዝብ እና ከአጋር ድርጅቶች ጋር ተጣምሮ የተፋጠነ ዕድገት እውን ለማድረግ እየተጋ መሆኑንም ተናግረዋል

መንግሥት ገቢን ለማሻሻል በርካታ ተግባራትን እያከናወነ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ "ከለውጡ በፊት የኢትዮጵያ ገቢ 170 ቢሊዮን ብር ብቻ ነበር፤ ነገር ግን መንግሥት በነደፋቸው ስትራቴጂዎች በዘንድሮው ዓመት ገቢው ከ1 ትሪሊዮን ብር በላይ ይጠበቃል፡፡ ይህ ትልቅ ለውጥ ነው" ብለዋል፡፡

"ያለፈው በጀት ዓመት ኢትዮጵያ በታሪኳ ከፍተኛ ገቢ ያገኘችበት ነው" ያሉም ሲሆን፤ ለአብነትም ከሸቀጦች ወጪ ንግድ 8 ነጥብ 3 ቢሊዮን ዶላር ተገኝቷል። ከሬሚታንስ 7 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ገቢ የተገኘ ሲሆን ገቢ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በመተካትም በቢሊዮን ዶላር ማዳን ተችሏል። በዚህም የኢትዮጵያ ሪዘርቭ በ10 እጥፍ አድጓል። ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም "የኢትዮጵያን ዕድገት ጥሩ አፍንጫ ያለው ሰው ከተማ ውጥስ ሲንቀሳቀስ በሽታ ያውቀዋል። ጥሩ ዐይን ያለው ሰው በማየት ብቻ ሊገነዘበው ይችላል፤ ጥሩ ጆሮ ያለውም ሰው በማድመጥ ሊረዳው ይችላል፤ የኢትዮጵያ ዕድገት የሚያጠራጥር ጉዳይ ስላልሆነ ወይ ዐይናችሁን፣ አፍንጫችሁን ወይም ጆሯችሁን መጠቀም ብቻ ነው የሚጠበቀው።" ሲሉ በምክር ቤቱ ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም የዋጋ ንረትን አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያ "መንግሥት የዋጋ ንረቱን ለማረጋጋት 440 ቢሊዮን ብር ድጎማ አድርጓል። ከዚህም ውስጥ 160 ቢሊዮን ብር የሚሆነው ለደሞዝ ጭማሪ፤ 140 ቢሊዮን ደግሞ ለነዳጅ ድጎማ እንደሚውል ገልጸዋል፡፡

በዚህም የጥቅምት ወር የዋጋ ንረት ወደ 11 ነጥብ 7 ወርዷል። ይህም ከሪፎርሙ ዘመን ጀምሮ ትንሹ የዋጋ ንረት ሆኖ ተመዝግቧል። በቀጣይም ይህን አሃዝ ወደ አንድ አሃዝ ለማውረድ ይሠራል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

አሁን ላይ ግን የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ሪፎርም በሁሉም መመዘኛዎች ከፍተኛ ለውጥ በፍጥነት ማስመዝገብ ችሏል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ