ጥቅምት 20/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ 7ኛው ሀገራዊ ምርጫ ግንቦት 24 እንደሚካሄድ መወሰኑን ተከትሎ “በሀገሪቱ ያለው ነባራዊ ሁኔታ ሀገራዊ ምርጫ ለማካሄድ ምቹ አይደለም" ሲሉ አሐዱ ያነጋገራቸው ተፎካካሪ ፓርቲዎች ገልጸዋል።

አሐዱ ያነጋገራቸው የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) እና እናት ፓርቲዎች "ቦርዱ ፖለቲካ ፓርቲዎችን ባወያየበት ዝግ ስብሰባ 'አስቻይ ሁኔታ የለም' የሚል ሐሳባችንን ብናንጸባርቅም ቦርዱ አልተቀበለውም ብለዋል።

የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ታጠቅ አሰፋ፤ "ሀገሪቱ አሁን ባለችበት ሁኔታ ምርጫ ማካሄድ እንመራዋለን የምንለውን ሕዝብ ለከፋ አደጋ ማጋለጥ ነው" ብለዋል።

አቶ ታጠቅ፤ "ምርጫ የዲሞክራሲያዊነት መገለጫ ቢሆንም መረጋጋት ይጠይቃል፡፡ በዚህ ሁኔታ ምርጫ ከማካሄድ ይልቅ አለመካሄድ ይመረጣል" ሲሉ የራሳቸውን እና የፓርቲያቸውን ሐሳብ ገልጸዋል፡፡

"እውነተኛና ፍትሓዊ ምርጫ ለማድረግ ምቹ ሁኔታ መፈጠር አለበት። አሁን ባለንበት ሁኔታ ምርጫ ይካሄድ ከተባለም ለአንድ ወገን ያደላ ነው" የሚል ስጋታቸውን ያስቀመጡት ኃላፊው፤ "ከሀገራዊ ምርጫ በፊት ሀገራዊ ሰላም ይቅደም" ብለዋል፡፡

Post image

በቀደመው ሐሳብ የሚስማሙት የእናት ፓርቲ የውጭ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ጌትነት ወርቁ በበኩላቸው፤ "ምርጫ ከማካሄድ በፊት ሕዝብ እና ሀገር ከገቡበት መከራ የሚመጡበትን መንገድ ማመቻቸት ይቀድማል" ብለዋል፡፡

ምርጫ መካሄዱ ግዴታ ከሆነም መንግሥት በቀረው አጭር ጊዜ የሚቻለውን ሁሉ አድርጎ አስቻይ ሁኔታዎችን ማመቻቸት እንደሚገባው አብራርተዋል፡፡

ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ይህን ቢሉም ኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ 7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ በተያዘው ዓመት ለማካሄድ ልዩ ልዩ የቅድመ-ምርጫ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡

ቦርዱ ጥቅምት 10 ቀን 2018 ዓ.ም የ7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ ረቂቅ የጊዜ ሠሌዳ በማስመልከት ከፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና ተወካዮች ጋር ምክክር ማድረጉም ይታወሳል።

ማክሰኞ ጥቅምት 18 ቀን 2018 በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በተመሳሳይ፤ "በያዝነው ዓመት መጨረሻ ሀገራዊ ምርጫ ይካሄዳል" ሲሉ ተደምጠዋል፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ