ጥቅምት 18/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) 7ኛው ሀገራዊ ምርጫን ለማከናወን መንግሥት በቂ አቅምና ዝግጁነት አለው ስለዚህም ይካሄዳል፤ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ጠንከር ብላቹ ወደ ምርጫ ግቡ ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ተናገሩ።
ኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ 7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ በተያዘው ዓመት ለማካሄድ ልዩ ልዩ የቅድመ-ምርጫ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል።
ከዚህም መካከል ቦርዱ ጥቅምት 10 ቀን 2018 ዓ.ም የ7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ ረቂቅ የጊዜ ሠሌዳ በማስመልከት ከፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና ተወካዮች ጋር ምክክር ማድረጉ ይታወቃል።
6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 2ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፤ "7ኛው ሀገራዊ ምርጫ ይካሄዳል" ሲሉ ማረጋገጫ ሰጥተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ "በጥቂት አካባቢዎች የሚረብሹ ጥቂት ሽፍታዎች አሉ ምርጫ አይካሄድም፤ ኤርትራ ምርጫ አይደረግም ብላለች ምርጫ አይደረግም ብለው የሚያስቡ ሰዎች አሉ" ሲሉ ተናግረዋል።
"ነገር ግን ምርጫ ይደረጋል እንዲሁም መንግሥት ምርጫን ለማድረግ በቂ አቅም አለው" ሲሉ፤ ምርጫ አይደረግም በሚል የሚነሱ ሃሳቦች ትክክለኛ አለመሆናቸውን ገልጸዋል።
"ሃሳብ አለኝ የሚል አካል በምርጫው መሳተፍ ይችላል" ያሉም ሲሆን፤ ምርጫው ከባለፈው የሚሻል እንደሚሆን ተናግረዋል።
ምርጫ አይደረገም በሚል እሳቤ 'ሕጋዊ መንግሥት የለም' በማለት 'የሽግግር መንግስት እንቋቁማለን' ብለው የሚያስቡ አካላት መኖራቸውን ገልጸዋል።
አክለውም ተፎካካሪ ፓርቲዎች "ጊዜው እንዳያመልጣችሁ ተዘጋጁና ተወዳደሩሩ እናዳያመልጣቹ አትሸወዱ ጠንከር ብላቹ ወደ ምርጫ ግቡ እንድታሸንፉ እንዲቀናቹ ምኞቴ ነው” ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
እንዲሁም የብልፅግና ፓርቲ አባላት 7ኛው ሀገራዊ ዴሞክራሲያዊ ብቻ ሳይሆን የተለያዩ ድምጾች የሚገኙበት እንዲሆን የሚሰራ መሆኑን አንስተው፤ "ጠቅልሎ የመውሰድ ፍላጎት እኛ ጋር የለም" ሲሉ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በ1992 ከኤርትራ ጋር በነበርው ውጊያ ምርጫ ማካሄድ መቻሏን ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ "ለመቀጠል የማንም ይሁንታ አያስፈልገንም በቂ አቅም አለን ምርጫ ይደረጋል" ብለዋል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ