ጥቅምት 14/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) ከህወሓት ተነጥለው የወጡ ከፍተኛ አመራሮች የመሰረቱት ዲሞክራሲያዊ ስምረት ትግራይ ፖርቲ የመመስራቻ ጉባኤውን በአዲስ አበባ በማካሄድ ላይ ይገኛል።

በኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ-ምግባር አዋጅ ቁጥር 1162/2011 ዓ.ም ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በተሰጠው ሥልጣን መሠረት፤ የክልላዊ የፖለቲካ ፓርቲ ጊዜያዊ የምዝገባ ፈቃድ ለዴሞክራሲያዊ ስምረት ትግራይ (ስምረት) ግንቦት 18 ቀን 2017 ዓ.ም መሰጠቱ ይታወሳል፡፡

Post image

በዚህም ፓርቲው በዛሬው ዕለት የመመስረቻ ጉባኤውን እያካሄደ ሲሆን፤ በጉባኤው ላይ የመክፈቻ ንግግር ያቀረቡት የፖርቲው መስራች አቶ ጌታቸው ረዳ በህወሓት ውስጥ በተፈጠረው ችግር ምክንያት አዲስ ፖርቲ ለመመስረት መገደዳቸውን ገልጸዋል።

አቶ ጌታቸው ፓርቲው በትግራይ ጉባኤውን ለማድረግ ፍላጎት የነበረው ቢሆንም በክልሉ ያለው ስርዓት አልበኝነት ጫፍ የደረሰ በመሆኑ ማካሄድ አለመቻሉን አስታውቀዋል።

ነገር ግን በቅርብ ጊዜያት ውስጥ ይህንን ጉባኤ በትግራይ ለማከናወን ማንም እንደማያግዳቸው ባደረጉት አጭር የመክፈቻ ንግግር ተናግረዋል።

በመመስረቻ ጉባኤው ላይ አቶ መለስ አለም ብልፅግናን በመወከል የተገኙ ሲሆን፤ ደሞክራሲያዊ ስምረት ትግራይ ፓርቲ ለምስረታ በመብቃቱ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ አዲስ የፖለቲካ መስመር ውስጥ መግባቷን፣ መግባባት እና መቀራረብ የሚችሉ ሀሳቦችን ወደ አንድ በማምጣት ፖርቲዎችን ወደ አንድነት አምጥቶ መስራት ማሳያ የሚሆን ነው ብለዋል።

Post image

ብልፅግና ፖርቲ የሀሳብ ልዩነቱን ጠብቆ ከዲሞክራሲያዊ ስምረት ትግራይ ጋር በአጋርነት ለመስራት ቁርጠኛ መሆኑንም አቶ መለስ አለም ተናግረዋል።

ሌላኛውና በጉባኤው ላይ ሀሳባቸውን የሰጡት የትግራይ ለውጥ ፈላጊ መስራች ሌተናል ጄነራል ፃድቃን ገብረትንሣኤ ናቸው።

ጄነራል ፃድቃን ይህ ጉባኤ ታሪካዊ መሆኑን የገለጹ ሲሆን፤ ለትግራይም ሆነ ለኢትዮጵያ አዲስ የፖለቲካ ሽግግር መሳያ ነው ብለዋል።

የትግራይ ችግር በዋነነት ከውጭ ሳይሆን በውስጥ በተፈጠረ ችግር የመጣ በመሆኑ ይህንን ለመለወጥ ለቆረጡና ለታገሉ ሁሉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

በቀድሞው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ የተቋቋመው የዲሞክራሲያዊ ስምረት ትግራይ (ስምረት) ፓርቲ፤ ነሐሴ 17 ቀን 2017 ሊያካሂድ ያሰበውን ጠቅላላ ጉባኤ ማድረግ ባለመቻሉ ላልተወሰነ ጊዜ ማራዘሙ ይስታወሳል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ