የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በጉጉት የሚጠበቀውንና ለሰባተኛ ጊዜ የሚካሄደውን ሀገር አቀፍ ምርጫ ለማከናወን ዝግጅቱን እያደረገ ይገኛል፡፡ ቦርዱ ይህንን ታላቅ ሀገራዊ ክንውን ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም. ለማካሄድ ዕቅድ ይዞ እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡

ቦርዱ የድምፅ መስጫ ዕለቱን፤ የምርጫ ቅስቀሳ ጊዜንና ሌሎችም ዝርዝር የምርጫ ሂደቶችን የያዘ ረቂቅ የጊዜ ሰሌዳ ማዘጋጀቱም ታውቋል፡፡ ይህንን ረቂቅ ሰነድ መሰረት በማድረግም ከፖለቲካ ፓርቲዎችና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ምክክር አድርጓል፡፡ ይሁን እንጂ ቦርዱ ያዘጋጀውን ይህንን የጊዜ ሰሌዳ ምክክር ከተደረገበት በኋላ እስካሁን በይፋ አላፀደቀውም፡፡

Post image

ይህ በእንዲህ እንዳለ፤ የቦርዱን ዝግጅትና በሀገሪቱ ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ አስመልክቶ ዘጠኝ የሚሆኑ ሀገር አቀፍና ክልላዊ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲሁም የፓርቲዎች ጥምረት ጠንከር ያለ መግለጫ አውጥተዋል፡፡

ፓርቲዎቹ ባወጡት የጋራ መግለጫ፤ የ2018 ዓ.ም. ጠቅላላ ምርጫ ከዚህ ቀደም በሀገሪቱ ከተካሄዱት ምርጫዎች የተለየ መልክ ሊኖረው እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

ምርጫው አስተማማኝ ሰላም ለመገንባት የሚያስችል መሆን እንዳለበትም አፅንኦት ሰጥተዋል፡፡ ይህ እንዲሆን ደግሞ ለምርጫው ምቹ ሁኔታን መፍጠር እንደ አንድ አማራጭ የሚታይ ሳይሆን፤ የግድ መሟላት ያለበት ቅድመ ሁኔታ መሆኑን አስምረውበታል፡፡

እነዚህ የፖለቲካ ድርጅቶች "መሰረታዊ" በሚል በመግለጫቸው የዘረዘሯቸው በርካታ ቅደመ ሁኔታዎች አሉ፡፡ የኢትዮጵያ መንግስትም በእነዚህ ጉዳዮች ላይ አፋጣኝና ተጨባጭ እርምጃዎችን እንዲወስድ አጥብቀው ጠይቀዋል፡፡

Post image

ተቃዋሚ ፓርቲዎቹ 'ለዲሞክራሲያዊ ምርጫ መካሄድ ወሳኝ ናቸው' ብለው ካመኑባቸውና በቅድመ ሁኔታነት እንዲሟሉ ከጠየቋቸው ጉዳዮች ውስጥ ቀዳሚው "ሁሉን አቀፍ የፖለቲካ ድርድር" ነው፡፡ ያለ ፖለቲካዊ መግባባትና ድርድር የሚደረግ ምርጫ ውጤቱ አመርቂ እንደማይሆን ያላቸውን ስጋት ገልፀዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች የሚስተዋሉ ግጭቶችና ውጊያዎች እልባት እንዲያገኙ ፓርቲዎቹ ጠይቀዋል፡፡ መግለጫውን ያወጡት ፓርቲዎች በሀገሪቱ ያሉ ሁሉም ግጭቶችና የትጥቅ ትግሎች ዘላቂ መፍትሄ ሊሰጣቸው እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

ባሳለፍነው ሳምንት ይህንን ጠንካራ መግለጫ በማውጣት አቋማቸውን ካንፀባረቁት መካከል ታዋቂ ፓርቲዎች ይገኙበታል። ከእነዚህም ውስጥ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ)፣ የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ)፣ የዐረና ትግራይ ለዲሞክራሲና ሉዓላዊነት (ዐረና ትግራይ) እና የዎላይታ ብሄራዊ ንቅናቄ (ዎብን) ተጠቃሽ ናቸው፡፡

የወላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ ሊቀመንበር አቶ አማኑኤል ሞጊሶ እንደተናገሩት፤ ሀገር በግጭት ውስጥ እያለች ምርጫን ለማከናወን መሞከር ተገቢነት የለውም፡፡ እንደ ሊቀመንበሩ ገለጻ፤ እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ዜጎች ላይ ተገቢ ያልሆነ ተጽዕኖ ይፈጥራል፡፡

Post image

በዋናነትም ዜጎች በዚህ አስቸጋሪ የጸጥታ ሁኔታ ውስጥ ሆነው ወደ ምርጫ እንዲመጡ ከተገደዱ፤ ውሳኔያቸው ነፃ ሊሆን አይችልም፡፡ ምናልባትም "ተቃዋሚዎች የሚመረጡ ከሆነ ግጭቶች ሊቀጥሉ ይችላሉ" ከሚል ፍርሃት በመነሳት፤ ምክንያታዊ ያልሆነና በነፃነት ያልተወሰነ ምርጫ እንዲያደርጉ ያስገድዳቸዋል፡፡ ይህ ደግሞ የምርጫውን ዴሞክራሲያዊነት ጥያቄ ውስጥ ይከተዋል፡፡

አቶ አማኑኤል እና ፓርቲያቸው ይህንን መግለጫ እንዲያወጡ ያስገደዳቸው ሌላኛው ወሳኝ ጉዳይ፤ በሀገሪቱ ሁሉን አካታች የሆነ ድርድር እንዲደረግ ያላቸው ጽኑ ፍላጎት ነው፡፡

ሊቀመንበሩ አሁን በሥራ ላይ ባለው የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ላይ ያላቸውን እምነት ማጣታቸውንም አልሸሸጉም፡፡ እንደ እሳቸው እምነት፣ ለሀገሪቱ የሚያስፈልጋት ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎችና ህዝቡ የሚተማመንበት የውይይት መድረክ ነው፡፡

በዚህ የጋራ መግለጫ ላይ የፈረሙትና አቋማቸውን የገለጹት ፓርቲዎች፤ ራሳቸውን ከምክክር ኮሚሽኑ ያገለሉ እንደሆኑ ይታወቃል፡፡ ፓርቲዎቹ በሰጡት ማብራሪያ፣ 'ምክክር ኮሚሽኑ የተቋቋመው ችግሮችን ለመፍታት ሳይሆን ምርጫን ለማራዘም ታስቦ የመጣ ነው' የሚል ጠንካራ ትችት አቅርበውበታል፡፡ ስለዚህም ኮሚሽኑ አሁን ባለበት ቁመና የሀገሪቱን ውስብስብ ችግሮች ይፈታል የሚል እምነት እንደሌላቸው በግልጽ ተናግረዋል፡፡

ባለፈው ሳምንት ይህንን የጋራ አቋም መግለጫ ካወጡት ፓርቲዎች መካከል ሌሎች አንጋፋና ወጣት ፓርቲዎችም ይገኙበታል።

የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢህአፓ)፣ የኢትዮጵያ ሶሻል ዲሞክራቲክ ፓርቲ (ኢሶዴፓ)፣ ህብር ኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (ህብር ኢትዮጵያ) እና ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ (ባልደራስ) ከፈራሚዎቹ መካከል ናቸው፡፡ እነዚህ ፓርቲዎች የጋራ አቋማቸውን በማንጸባረቅ መንግሥት ቆም ብሎ እንዲያስብ ጠይቀዋል፡፡

ከእነዚህ ፓርቲዎች መካከል የህብር ኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ ግርማ በቀለ ለአሐዱ ሬዲዮ ሀሳባቸውን አጋርተዋል፡፡ አቶ ግርማ እንደሚሉት፤ በኢትዮጵያ ውስጥ የመንግሥት ለውጥ መምጣት ያለበት በምርጫ ብቻ መሆኑን ፓርቲያቸው በጽኑ ያምናል፡፡

Post image

ከምርጫ ውጪ ሌላ አማራጭ መንገድ የለም፤ የሚመጣው ለውጥም ሕጋዊና ሰላማዊ መሆን አለበት፡፡

አቶ ግርማ አክለውም፤ መግለጫው ያነጣጠረው ምርጫው "አስቻይ ሁኔታ" (Enabling Environment) ሊኖረው ይገባል በሚለው ጉዳይ ላይ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ምርጫ ማድረግ ብቻውን ግብ አይደለም፤ የምርጫው ሜዳ ለሁሉም እኩልና ሰላማዊ መሆን አለበት፡፡ ይሁን እንጂ አሁን ባለው ሁኔታ ፓርቲዎቹ ገና ወደ ቦይኮት (ምርጫውን ወደ መተው) ውሳኔ አልገቡም፡፡ "ቅድመ ሁኔታው አሁኑኑ ካልተሳካ ምርጫ አንገባም" ወደሚል የመጨረሻ ውሳኔ ላይ የሚያስደርስ ደረጃ ላይ ገና አልደረስንም ሲሉ አሁን ያሉበትን የትግል ምዕራፍ አብራርተዋል፡፡

የፌዴራል መንግሥት በበኩሉ፤ በሀገሪቱ በሁሉም አቅጣጫ ያሉ ግጭቶች እንዲቆሙ ፍላጎት እንዳለው በተደጋጋሚ ጊዜ ሲገልፅ ቆይቷል፡፡

በተለይም ከትግራይ ክልል ጋር በነበረው ደም አፋሳሽ ጦርነት በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት መቋጫ እንደተገኘ ሁሉ፤ ሌሎች ግጭቶችንም በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ቁርጠኛ ነኝ ሲል ይደመጣል፡፡ ይሁን እንጂ ይህ የመንግሥት ቃል በተግባር ምን ያህል ታይቷል? የሚለው የፓርቲዎቹ ጥያቄ ነው፡፡

ይህንን የመንግሥትን አቋም አስመልክቶ አቶ ግርማ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ እንደ እሳቸው ገለጻ፤ ስምምነቶችና የሰላም ጥሪዎች እንዲሁ ለይስሙላ የሚደረጉ መሆን የለባቸውም፡፡

ስምምነቶች ከልብ የመነጩና እውነተኛ ፍላጎትን መሰረት ያደረጉ መሆን አለባቸው፡፡ ነገሮች በዚህ መንገድ የሚታዩ ከሆነና ሁሉም አካል ግጭቶችን ለማቆም በቀና ልብ የሚንቀሳቀስ ከሆነ፣ በሀገሪቱ ያሉ ግጭቶችን በአጭር ጊዜ ማቆም የሚቻል መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ዋናው ቁልፍ ያለው በቅንነትና በቁርጠኝነት ላይ መሆኑን አስምረውበታል፡፡

በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ፓርቲ (ኢህአፓ) የውጭ ጉዳይ ኃላፊ የሆኑት አቶ እስክንድር ሞገስም፤ ጠንከር ያለ ሀሳብ ሰንዝረዋል፡፡

Post image

አቶ እስክንድር እንደሚሉት፤ በግጭትና በጦርነት ውስጥ ሆኖ ስለ ድርድርና ውይይት ጥሪ ማድረግ እርስ በርስ የሚጣረስ ጉዳይ ነው፡፡ እነዚህ ሁለት ነገሮች አብረው ሊሄዱ አይችሉም፡፡ መንግሥት የሰላም ሆነ የውይይት ጥሪ ለማድረግ ከፈለገ፣ በቅድሚያ ራሱን ከግጭት መድረክ ማግለል ይኖርበታል፡፡

አቶ እስክንድር ንግግራቸውን በመቀጠል፤ በሀገሪቱ ችግሮች ዙሪያ ጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጦ ለመወያየት ሊሟሉ የሚገቡ ቅድመ ሁኔታዎችን ዘርዝረዋል፡፡

እንደ እሳቸው እምነት፤ በቅድሚያ ግጭቶች መቆም አለባቸው፣ በመቀጠልም በፖለቲካ ምክንያት የታሰሩ ኃይሎችና ግለሰቦች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ መፈታት ይኖርባቸዋል፡፡ የውይይት መድረክ ሲዘጋጅ ለእነዚህ አካላትም ክፍት መሆን አለበት፡፡

ይህ ሀገር የሁሉም ኢትዮጵያዊ እስከሆነ ድረስ፣ የሚደረገው ውይይት ሁሉን አካታች መሆን አለበት፡፡ አቶ እስክንድር በመግለጫው ላይ ቅድመ ሁኔታ እንዲቀመጥ የተደረገበት ዋና ምክንያትም ይኸው እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡

Post image

አሁን የተቋቋመውና እየሰራ ያለው የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሁሉንም የፖለቲካ ኃይሎች ማሳተፍ ነበረበት፡፡ ነገር ግን ይህ ባልሆነበትና ብዙዎች በተገለሉበት ሁኔታ በሂደቱ ተሳትፎ ማድረግ፤ ለተሳሳተ ጉዳይ ተባባሪ እንደመሆን ይቆጠራል ሲሉ ምክክር ኮሚሽኑን አጥብቀው ኮንነዋል፡፡

መግለጫውን ያወጡት እነዚህ ዘጠኝ ፓርቲዎች፣ መንግሥት ለምርጫ የሚሆን አስቻይና ምቹ ሁኔታ እስኪፈጥር ድረስ ጥሪያቸውን ከመጠየቅ እንደማይቦዝኑ ገልጸዋል፡፡

Post image


ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ በወጣው መግለጫ የመጨረሻ ሳይሆን የትግላቸው አካል ነው ያሉት ፓርቲዎቹ፤ በቀጣይም የተለያዩ ሕጋዊና ሰላማዊ ስልቶችን በመጠቀም መንግሥት ላይ ጫና መፍጠራቸውን እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል፡፡

ዓላማቸውም መንግሥት ከግጭት ነፃ የሆነችና የሰከነች ሀገር ፈጥሮ፤ ሁሉም ዜጋ በነፃነት የሚሳተፍበት፣ ሁሉን አካታች የሆነ ምርጫ እንዲደረግ ማስቻል መሆኑን ተናግረዋል፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ