ሕዳር 8/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) እስራኤል የኢትዮጵያን የዓባይ ውሃ አጠቃቀም እና የወደብ ተጠቃሚነት ጥያቄ ትደግፋለች ሲል በእስራኤል የኢትዮጵያ ኤምባሲ አስታውቋል።
በእስራኤል የኢትዮጵያ አምባሳደር ተስፋዬ ይታይህ ለአሐዱ ሬዲዮ እንደተናገሩት፤ አብዛኛው የኤምባሲው ሥራ የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም ማራመድ ላይ ትኩረቱን ያደርጋል።
ስለዚህ አንዱ ብሔራዊ ጥቅም ከዓባይ ውሃ አጠቃቀም እና ከኢትዮጵያ የወደብ ጥያቄ ጋር የተያያዘ በመሆኑ፤ በእነዚህ ሁለት ጉዳዮች ላይ በዋናነት ትኩረት ሰጥተን እየሰራን እንገኛለን ብለዋል፡፡
"በታሪክ ወደኋላ ተመልሰን ስናይ እስራኤል ኢትዮጵያ ወደብ አልባ እንዳትሆን ስትሰራ ነበር" ያሉት አምባሳደሩ፤ "ይህም ለኢትዮጵያ ጥቅም ብቻ ሳይሆን ለራሷም ብላ የምታደርገው ነበር።" ብለዋል፡፡ "ኢትዮጵያ ከወደብ ተጠቃሚነት በተገፋች ቁጥር ቀይ ባህር የአረብ ሀገራት የበላይነት ይነግስበታል፡፡ ይህ ደግሞ ጉዳቱ ለእስራኤልም ጭምር ነው" ሲሉ አስረድተዋል፡፡

እስራኤል ከቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት ጀምሮ በወታደራዊ ስልጠና ኢትዮጵያን ስታግዝ እንደነበር በመግለጽም፤ በወቅቱ "ነበልባል" የተሰኘ ጦር በእስራኤሎች መሰልጠኑን አስታውሰዋል። በተጨማሪም አየር ኃይልን የማጠናከር ሥራ በእስራኤል መሰራቱን ገልጸዋል።
"ኤርትራ ከኢትዮጵያ የተነጠለች ነጻ ሀገር መሆኗን ተከትሎም፤ ኢትዮጵያ ከሁለት ወደቦች ማለትም ከምጽዋ እና አሰብ ባለቤትነት ወደ ወደብ አልባ ሀገርነት ተቀየረች" ብለዋል።
በተጨማሪም በደርግ ጊዜም ሆነ እ.ኤ.አ ከ1973 በኋላ የሁለቱ ሀገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ተቋርጦ እንደነበር ያስታወሱት አምባሳደር ተስፋዬ፤ ሆኖም ከወታደራዊው ደርግ መንግሥት ጋር ይፋ የማይወጣ በወታደራዊና በመረጃ ልውውጥ የመተባበር ግንኙነት እንደነበር ተናግረዋል።
አሁን ላይ ኢትዮጵያ በሕጋዊ፣ ሰላማዊ እና ዲፕሎማሲያዊ መንገድ በሰጥቶ መቀበል መርህ የባህር በር ባለቤት ለመሆን ጥረት እያደረገች መሆኑን በማንሳት፤ ኤምባሲው ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ ይህን የኢትዮጵያን ጥያቄ በማስረዳት ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ስለዚህ "በእስራኤል በኩል ኢትዮጵያ የባህር በር የማግኘት ጥያቄዋን የመቃወም ሁኔታ የለም" ሲሉ ከአሐዱ ለተነሳላቸው ጥያቄ ምላሽ ሰጥተዋል።
ይህንንም ሲያብራሩ፤ "ኢትዮጵያ እንደገና መልሳ ወደ ቀይ ባሕር ጠረፍ ብትመጣ አንደኛ ወዳጅ ሀገር ናት፤ በተጨማሪም እስራኤል ኢትዮጵያን መግቢያ በር አድርጋ ስለምትመለከታት ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ጋር ያላትን ግንኙነት ለማጠናከር እንድታግዛት ትፈልጋለች" ብለዋል።
"እስራኤላውያን ኢትዮጵያን የሚያዩበት መንገድ የተለየ ነው" ያሉት አምባሳደር ተስፋዬ፤ "በተጨማሪም በአፍሪካ ሕብረት የተመልካችነት ድርሻን መልሶ ለማግኘት የእኛን ድጋፍ ይሻሉ" ሲሉ ገልጸዋል።
አክለውም፤ ኢትዮጵያ በተለያዩ ዘርፎች ሰፊ የልማት አቅም ያላት ሀገር በመሆኗ፤ 'በዚህ ውስጥ በመሳተፍ እኛም እንጠቀማለን' ብለው እንደሚያስቡ አብራርተዋል፡፡
ስለዚህ የኢትዮጵያን ጥያቄዎች የመደገፍ እንጂ ለምን እና እንዴት? የሚለውን ነገር አያነሱም ሲሉ ተናግረዋል።
"ኢትዮጵያ አሁን ያነሳችውን የባህር በር ጥያቄ የእስራኤል መንግሥት ይደግፈዋል ግን አሁን በኢትዮጵያ ጉዳይ መግለጫ መስጠት አይችልም" ያሉት አምባሳደሩ፤ "ሁኔታው እያደገ ሲሄድ ድጋፉን ይገልጻል ተብሎ ይጠበቃል። በዚህም ጉዳይ እየተነጋገርን ነው" ብለዋል።
አምባሳደር ተስፋዬ አክለውም፤ በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ዙሪያ ግብጾች መጀመሪያ ግድቡ እንዳይሰራ ጥረት ሲያደርጉ እንደነበር ገልጸው፤ ነገር ግን ኢትዮጵያ በራሷ አቅም ግንባታውን አጠናቃ ማስመረቋን አስታውሰዋል።
"ግብጾች የሚያነሷቸው ጥያቄዎች መሰረተ ቢስ ናቸው" ያሉም ሲሆን፤ ኢትዮጵያ ፍትሃዊነትን ለማረጋገጥ የሄደችበት መንገድ እንዲሁም ጉዳዩን በበቂ ሁኔታ በዓለም አቀፍ መድረኮች እያስረዳች ስለመጣች 'አሁን ድርድሩ ውጤት ስላላመጣልን ትተነዋል' የሚል አቋም መያዛቸውን አስረድተዋል።
"ከዚያ ውጪ ግን በዚህ ዓመት ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ደብዳቤ ጽፈው ነበር ለዚያም አጥጋቢ መልስ ተሰጥቷል" ብለዋል።
"በዚህም ዓለም የእኛ እውነት እየገባው ነው" ያሉ ሲሆን፤ ዋናው ነገር ግድቡ ተጠናቆ ኃይል ማመንጨት መጀመሩ ነው። የተወሰኑ ተግዳሮቶች ይኖራሉ እነሱን ደግሞ በተለመደው መልኩ እየተቋቋምን ራሳችንን እያጠነከርን እንሄዳለን ብለዋል።
በሌላ በኩል በእስራኤል የሚገኙ ቤተ-እስራኤላውያ ከ175 ሺሕ እስከ 180 ሺሕ እንደሚገመቱ የገለጹት አምባሳደሩ፤ ይህም በሁለቱ ሀገራት መካከል የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱን ለማሳደግ ትልቅ ሚና እንዳለው አስረድተዋል።
በእስራኤል የተለያዩ ከተሞች የኢትዮጵያ ባህላዊ መገለጫ የሆኑ መደብሮች እና ሬስቶራንቶች መኖራቸውን ገልጸው፤ በእነርሱም አማካኝነት የኢትዮጵያን ባህላዊ ምግቦች፣ አልባሳት እና ቋንቋ የማስተዋወቅ ሥራ እንደሚሰራ አብራርተዋል።
በተጨማሪም፤ በኢትዮጵያ የሚገኙ እስራኤላዊያን በተለያዩ የልማት እና የኢንቨስትመንት ሥራዎች ላይ እንደሚሳተፉ በማንሳት፤ ኤምባሲው በኢትዮጵያ ያሉ የንግድ፣ የኢንቨስትመንት እና የቱሪዝም እድሎችን ለእስራኤላውያን የማስተዋወቅ ሥራ እንደሚሰራ ገልጸዋል።
ይህም የሁለቱን ሀገራት የእርስ በእርስ ግንኙነት ይበልጥ እያጠናከረው እንደሚገኝ ነው ብለዋል፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ