ሰኔ 26/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የመርሲሳይዱ ክለብ ሊቨርፑል የፊት መስመር ተጫዋች የሆነው ፖርቹጋላዊው ዲያጎ ጆታ ንጋት አካባቢ ባጋጠመው የመኪና አደጋ ሕይወቱ ማለፉን ማርካ አስነብቧል።
ዛሞራ በተባለ አካባቢ በተከሠተው የመኪና አደጋ ህይወቱ እንዳለፈ የተገለጸው ዲያጎ ጆታ፤ አብሮት የነበረው ወንድሙም ሕይወቱ ማለፉ ተገልጿል።

የ26 ዓመቱ የጆታ ታናሽ ወንድም አንድሬ ሲልቫም ልክ እንደ ወንድሙ ሁሉ ፕሮፌሽናል እግር ኳስ ተጫዋች የነበረ ሲሆን፤ በፖርቱጋል ሁለተኛ ሊግ ለሚሳተፈው ፔናፌል በመጫወት ላይ ይገኝ ነበር።
የ26 እና የ29 ዓመት እድሜ ያላቸው ወንድማማቾቹ በጉዞ ላይ እንዳሉ አደጋ የገጠማቸው ሲሆን፤ መኪናውም በእሳት የተያያዘ መሆኑ ሲገለፅ አደጋውም ከበድ ያለ ነው ተብሏል።

የሊቨርፑሉ ኮከብ ከአምስት ቀን በፊት የሠርግ ሥነ-ስርዓቱን በእስፔን ማከናወኑ ይታወሳል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ