ጥቅምት 29/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በዐዋጅ የተሰጠውን ሥልጣን በመጠቀም፣ በአቶ ጌታቸው ረዳ ካሕሳይ አመራር የቀረበለትን የአዲስ ክልላዊ የፖለቲካ ፓርቲ የምዝገባ ጥያቄ ለሕዝብ ይፋ ማድረጉን አስታውቋል፡፡
በዚህም መሠረት ክልላዊ የፖለቲካ ፓርቲ የምዝገባ ጥያቄ ያቀረበው ፓርቲ "ዴሞክራሲያዊ ስምረት ትግራይ (ስምረት)" በሚል ስያሜ ሲሆን፤ በእንግሊዝኛ ደግሞ "Tigray Democratic Solidarity Party (Solidarity)" የሚል ስያሜ እንዳለው ቦርዱ ገልጿል።
በመሆኑም እነአቶ ጌታቸው ረዳ ካሕሳይ "ዴሞክራሲያዊ ስምረት ትግራይ (ስምረት) ወይም Tigray Democratic Solidarity Party (Solidarity)" ፓርቲ ሥም፣ ዐርማ ወይም ሌሎች ጉዳዮች ላይ ተቃውሞ ያለው ሰው፤ ከዛሬ ከጥቅምት 29 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በ14 ቀናት ውስጥ ተቃውሞውን ለቦርዱ ጽሕፈት ቤት እንዲያቀርብ ቦርዱ አሳውቋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ "በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ማቋቋሚያ ዐዋጅ ቁጥር 1133/2011" እና "በኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና የምርጫ ሥነ-ምግባር ዐዋጅ ቁጥር 1162/2011" መሠረት የፖለቲካ ፓርቲዎችን የመመዝገብ ኃላፊነት እንደተሰጠው ይታወቃል፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
ምርጫ ቦርድ የጌታቸው ረዳን 'ዴሞክራሲያዊ ስምረት ትግራይ' ፓርቲ የምዝገባ ጥያቄ ለሕዝብ ይፋ አደረገ
በፓርቲው ሥም፣ ዐርማ ወይም ሌሎች ጉዳዮች ላይ ተቃውሞ ያለው ሰው በ14 ቀናት ውስጥ ማቅረብ ይችላል ተብሏል