ጥቅምት 13/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን የብቃት ማረጋገጫ እና ዕውቅና ሳይሰጣቸው በማምረት ሥራ ላይ የተሰማሩ፤ ከ70 በላይ የዘይት አምራች ድርጅቶች ላይ እርምጃ መውሰዱን ለአሐዱ አስታውቋል።
የባለሥልጣኑ የእንስሳት ተዋጽኦና አልሚ ምግብ ዴስክ ኃላፊ አቶ መሐመድ ሁሴን፤ እርምጃው የተወሰደባቸው አምራቾች ደረጃቸውን ያልጠበቁ፣ ጥራት የጎደላቸውና ደኅንነታቸው ያልተረጋገጠ የዘይት ምርቶችን የሚያመርቱት ላይ እንደሆነ ገልጸዋል።
ኃላፊው ይህ ሕገ-ወጥ አካሔድ በሕብረተሰቡ ጤና ላይ ከፍተኛ ችግር ከማስከተሉ ባሻገር፤ ከሕግ ውጭ የሚፈጸም አሠራር መሆኑን አብራርተዋል።
"ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ከክልሎችና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ቁጥጥርና ክትትል የሚያደርግ ግብረ-ኃይል በማቋቋም ሥራው በስፋት እየተከናወነ ይገኛል" ብለዋል።
በተጨማሪም፤ በሀገር ውስጥ የሚመረቱ ዘይቶችን ከውጭ የገቡ አስመስለው በሐሰተኛ ሥምና አርማ ለገበያ ሲያቀርቡ የነበሩ ሕገ-ወጥ ነጋዴዎችና ድርጅቶች ላይም እርምጃ እየተወሰደ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ኃላፊው አቶ መሐመድ፤ ደኅንነታቸው ያልተረጋገጠ የሀገር ውስጥ የዘይት ምርቶችን ከውጭ ከሚገቡ ምርቶች ጋር በሽፋን በማመሳሰል ሲሸጡ በነበሩ ጥፋተኞች ላይም እርምጃ ተወስዷል ብለዋል።
በማኅብረተሰብ ጥቆማ መሠረት የተወሰደው እርምጃ፤ የጹሑፍ ማጠንቀቂያን ጨምሮ የፈቃድ መሰረዝ እንዲሁም በሕግ መጠየቅን እንደሚያካትት ተናግረዋል።
የብቃት ማረጋጫና እውቅና ሳይሰጣቸው ማንኛውም ምርት ማምረት እንደማይቻልና በሕገ-ወጥ ተግባር የተገኙትንም የማያዳግም እርምጃ እንደሚወስድም ኃላፊው አጽንኦት ሰጥተውበታል።
አክለውም ሕገ-ወጥ ነጋዴዎቹ ቦታና ስያሜ መቀያየርን ጨምሮ የተለያዩ የማጭበርበሪያ ዘዴዎችን እንደሚጠቀሙ ገልጸው፤ ሕብረተሰቡ ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያደርግ እንዲሁም ስለ ጉዳዩ ጥቆማ እንዲሰጥ ጥሪ አቅርበዋል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
ከ70 በላይ የዘይት አምራች ድርጅቶች በአሰራር ግድፈት ምክንያት መቀጣታቸው ተገለጸ
የሀገር ውስጥ ምርትን ከውጭ የገባ በማስመሰል የሸጡ ግለሰቦች እና ድርጅቶችም እርምጃ ተወስዶባቸዋል ተብሏል