ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ "ያለ ፍልሚያ ለውጥ እና ሰላም አይመጣም" ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ያሉት ከሰሞኑ በባሌ ዞን የሱፍ ኡመር ዋሻ ውስጥ በተካሄደ 'የሶፍ ዑመር ወግ' በተሰኘ ውይይት ላይ ነው፡፡

በመንግሥት መገናኛ ብዙኃን በተሰራጨው በዚህ ውይይት የቀድሞ የህወሓት/ ኢህአዴግ አመራሮች እና ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸውን ጨምሮ ሌሎችም የመንግሥት ባለስልጣናት ተሳትፈዋል፡፡

Post image

ዋነኛ ትኩረቱን የተፈጠርሮ ፀጋን በመጠቀም እና በሰላም ዙሪያ ባደረገው በዚህ ውይይት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አክሱም በጣልያን መንግሥት፣ ላሊበላ በፈረንሳይ መንግሥት እገዛ የእድሳት ሥራቸው እንደተከናወነ ገልጸዋል፡፡

የላሊበላን እድሳት በታቀደለት ጊዜ እንዳይጨርሱ "አደናቃፊዎች" ሲሉ የጠራቸው ኃይሎች እንቅፋት ስለመሆናቸው አብራርተዋል፡፡

ሰኞ ጥቅምት 10 ቀን 2018 ዓ.ም በመንግሥት መገናኛ ብዙኃን የተላለፈውና ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር ወደ ባሌ ዞን የተጓዙ የመንግሥት ኃላፊዎች እና የቀድሞ የኢህአዴግ ባለሥልጣናት የተሳተፉበት ነው።

ሁለት ሰዓት ገደማ የሚጠጋው ይህ ውይይት በአብዛኛው ያተኮረው በባሌ ዞን የሚገኙ የተፈጥሮ ሀብቶችን ማልማት እና መጠቀምን በተመለከተ ነው።

በውይይቱ ላይ የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን፣ የቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር ሚኒስትር አብርሃም በላይ (ዶ/ር) ተሳትፈዋል።

Post image


በተጨማሪም የጠቅላይ ሚኒስትሩ የምሥራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ ጌታቸው ረዳ፣ የማክሮ ኢኮኖሚ አማካሪ አምባሳደር ግርማ ብሩ እና የማኅበራዊ ጉዳዮች አማካሪ ዳንኤል ክብረት ተገኝተዋል።

የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳም እንዲሁም የቀድሞው የክልሉ መሪዎች አባዱላ ገመዳ፣ ኩማ ደመቅሳ፣ ጁነዲን ሳዶ እና ወርቅነህ ገበየሁም የውይይቱ አካል ነበሩ።

Post image

የቀድሞው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ መስተዳድር ምክትል ፕሬዝዳንት ሌተናንት ጄነራል ጻድቃን ገብረትንሳኤም ከተሳተፉት መካከል ናቸው።

በውይይቱ ላይ የተሳተፉት የቀደሞ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አመራሮችን ጨምሮ፤ የኢህአዴግ ከፍተኛ ኃላፊዎች የነበሩም በውውይቱ ላይ ተሳትፈዋል።

በውይይቱ ላይ የቀድሞውም ሆኑ አዲሶቹ አመራሮች በተመለከቱት ለውጥ መደነቃቸውን ገልጸዋል።

የብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን "እጥረት ያባላል ያጋጫል" ያሉ ሲሆን፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ግን መትረፍ እና ፀጋ ነው የሰላማችን ጠንቅ የሆነብን ሲሉ በውይይቱ ላይ ሀሳባቸውን ሰንዝረዋል።

የተፈጥሮን ሀብት ተመልክተናል ያሉ ሲሆን፤ በተፈጥሮ ጋር ተርቆ መኖር እንደሚቻል አይተናል ሲሉ በባሌ የተመለከቱትን ተፈጥሮ ያደንቃሉ።

ይህንን መሰሉ ወይይት ጠቅላይ ማኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከከፍተኛ አመራሮች ጋር በመሆን በሀላባ፣ ከንባታ እና ስልጤ ጨምሮ ማካሄዳቸው የሚታወስ ነው።

በውይይታቸዉ ወቅትም በቤት ልማት ዙሪያ ሰፋ ያለ ሀሳቦች ተነስተዋል።

በሰሞኑ በሶፍ ዑመር ዋሻ ውስጥ በተደረገው ወይይት ላይ አሁን ያሉንን ፀጋዎች ለመጠቀም ሰላም መረጋገጥ ቁልፍ መሆኑ ተነስቷል።

የቀድሞ የትግራይ ክልል ጊዚያዊ አስተዳደር ምክትል ፕሬዝዳንት ሌተናል ጄነራል ጻድቃን ገብረትንሣኤ "ሰላማችንን ጠበቅን መሄድ ከቻልን ብሩህ ጊዜ ከፊታችን አለ" ብለዋል።

Post image

"ያሉብን ችግሮችን ለመፍታት 'እኔ ያልኩት ብቻ ይሁን' ከሚል እሳቤ እየወጣን ለሀገር የሚጠቅም ነገሮችን መስራት አለብን" ሲሉም አንስተዋል።

በውይይቱ ሌላዉ ተናጋሪ የነበሩት የጠቅላይ ሚኒስተሩ የምሥራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ ጌታቸዉ ረዳ ናቸው።

እንደ አማካሪዉ ገለፃ "እምቅ ሀብት እያለን አቅሙም ባለበት ሁኔታ ባለመስራታችን መደህየታቸን አሳዛኝ ነው" ሲሉ ይቆጫሉ።

ያለፉትን ውድቀቶች በመመርመር ያለንን አቅም በመፈተሽ በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች ተመሳሳይ ሥራዎች መሰራት እንዳለባቸውም አንስተዋል።

Post image

አቶ ጌታቸው ረዳ ወደ ፌደራል መንግሥት ከመጡ ወዲህ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በሚሄዱባቸው ጉብኝቶች ላይ ቀዳሚው ሰው ሆነው ተገኘተዋል፡፡

የጠቅላይ ሚኒሰትሩ አማካሪ ባሌ ከመጡ 13 ዓመት እንዳላፋቸው የገለጹም ሲሆን፤ እሳቸው ሲመጡ አንድ አስፋልት ብቻ እንደነበር በውይይቱ ላይ አንስተዋል፡፡

ሀሳባቸውንም ሲጨምሩ የቱሪስት መዳረሻ የሆኑ አካባቢዎች ከመልካዓ ምድር በላይ ታሪካዊነት ያላቸው መሆናቸውም መገንዘብ አለብን ብለዋል፡፡

በዚህ የባሌው ጉብኝት ከሶፍ ዑመር በተጨማሪ የተለያዩ ፕሮጀክቶችም ምረቃት መርሀ ግብር ተከናውኗል፡፡

በሶፍ ዑመር ዋሻ ውስጥ በነበረው ውይይት ላይ ሰፋ ያ ለጊዜ ወስደው ሀሳባቸውን ሰነዘሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፤ "ከታሪክ ጋር ፀብ አይኑረን ስንል ቆይተናል" ብለዋል፡፡

Post image

አክሱምን በጣልያን መንግሥት ላሊበላን ደግሞ በፈረንሳይ መንግሥት እገዛ እድሳቱን አከናውነነው ለመጨረስ ተቃረብን ነበር ብለዋል፡፡

"ይሁን እንጂ የላሊበላን እድሳት ለመጨረስ "አደናቃፊዎች" ሲሉ የጠራቸው ኃይሎች ለመጨረስ አላስቻሉንም" ሲሉ ገልጸዋል፡፡

በወይይቱ ላይ ከቀድሞ አህአዴግ አራቱ ብሔራዊ ድርጅቶች መካከል ከብአዴን ተወካዮች ውጪ ሁሉም መሳታፈቻውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይገልጻሉ፡፡

ይህ ዓይነቱ ስብስብ ወደ ውይይት መማጣት ከተቻለ ላለመወያየት የሚያደርጉን ነገሮችን መለየት ያስፍልጋል ሲሉም ተደምጠዋል፡፡

በተወያዮች ስለሰላም ጥያቄ እና ሀሳብ ቀርቦላቸው የነበረም ሲሆን፤ ይህንንም ሲለመልሱም "ያለፍልሚያ ፈጠራ ዕውን መሆን አይችልም" ብለዋል፡፡

ከሰሜን እስከ ደቡብ ባለው የሀገሪቱ ክፍሎች 'ልገንጠል' በሚል የተደራጁ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዳሉ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ "አንዱም ሀገሩን አያውቅም" ሲሉ ተችተዋል፡፡

"ኢትዮጵያ ውስጥ ሽፍታ ጠፍቶ አያውቅም" ያሉም ሲሆን፤ ሽፍታ ለመሳደድ የደከሙ መሪዎች ሶፍ ዑመርን አያውቁትም ሲሉም ጠንከር ያለ ሀሳብ ሰንዝረዋል፡፡

"ሽፍታውን በአንድ እጃችን እያጠፋን ልማት ካለሰራን የምንመኘውን ዓይነት ሰላም ማምጣት አንችልም" ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ገልጸዋል፡፡

በሶፍ ዑመር እድሳት እና ማሻሻያ በኃላ ውይይት ያደረጉት የቀድሞውም አዲሶቹም አመራሮች ያዩትን ሥራ አድንቀዋል፡፡

Post image

ይሁን እንጂ ይህ ልማት በሁሉም አከባቢዎች ተደራሽ መሆን ካለበት እንደሀገር ያሉ ሰላም መደፍረሶች መፈታት እንዳለባቸው፤ በተለይም የቀድሞ የትግራይ ምክትል ፕሬዝዳንት ፃቃን ገብረትንሳኤ እና የቀድሞ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ኩማ ደመቅሳ ጠይቀዋል፡፡

ለዚህም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ "ያለፍልሚያ ለውጥ እና ሰላም አይጣም" የሚል ምላሽ ሰጥተውበታል፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ