ጥቅምት 13/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) ገንዘብ ሚኒስቴር ኢትዮጵያ በውሃ ቱሪዝም እንቅስቃሴ ያላትን ተሳትፎ እንድታሳድግ በማሰብ ለአንድ ዓመት ብቻ ጀልባዎች ቀረጥ ሳይከፈልባቸው ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ ቢፈቅድም፤ እስከ አሁን ይህንን ዕድል የተጠቀሙ ባለሃብቶች እንደሌሉ ተገልጿል።

በዘርፉ የተሰማሩ ባላሃብቶች ለአንድ ዓመት የሚቆየውን ዕድል እንዲጠቀሙ ያሳሰበው ቱሪዝም ሚኒስቴር፤ ይህ አሰራር የጎብኚዎችን የቆይታ ግዜ እንዲራዘም ዕድል እንዲፈጥር የታለመ ነው ብሏል።

የቱሪዝም ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት እና ኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈፃሚ አቶ ዓለማየሁ ጌታቸው፤ "የመዝናኛ ጀልባዎችን ከቀረጥ ነጻ ወደ ሀገር ውስጥ መግባታቸው ኢትዮጵያ ከቱሪዝም የምታገኘውን ገቢ የምታሳድግበትን መልካም አጋጣሚ ይፈጥራል" ብለዋል።

ከቀረጥ ነፃ የሚገቡት ልዩ ልዩ ጀልባዎች የውሃ ላይ ምርምር ለማድረግ እና የአሳ ሃብትን ለማሳደግ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳላቸውም ለአሐዱ ገልጸዋል።

በቱሪዝም ዘርፉ የተሰማሩ ሆቴሎች እና አስጎብኚ ድርጅቶች ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ፍቃድ ጠይቀው ጀልባዎችን ከቀረጥ ነጻ የማስገባት ዕድሉን እንዲጠቀሙበት ጥሪ አቅርበዋል።

የሚዲያ አካላት ከዓለም አቀፍ ተሞክሮዎች በማየት ዘርፉ ለሀገራችን የቱሪዝም ዘርፍ አዲስ በመሆኑ ግንዛቤ የመፍጠር ሥራን ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጋር በመተባበር እንዲሰሩም ሥራ አስፈፃሚው ጠይቀዋል።

የሚገቡት ጀልባዎች የውሃ ላይ ቱሪዝምን ከማስፉት በተጨማሪ የሥራ ዕድል እንደሚፈጥሩ አንስተው፤ በዘርፉ ከውሃ ጋር ተያይዞ የሚፈጠር አደጋን የሚከላከሉ ሰዎች ተጨማሪ የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር አስታውቀዋል።

ከአሳ ምርት በተጨማሪ፤ ተጨማሪ ምግብ ለማቅረብ የሚረዱ ጀልባዎችን ማስገባት እንደሚቻልም ተገልጿል።

የሀገር ውስጥ እና የውጭ ቱሪዝምን በመሳብ ረገድ ሊያገለግሉ የሚችሉ በሀገራችን የተለያዩ አካባቢዎች ከ20 በላይ ታላላቅ ሐይቆች ያሉ ሲሆን፤ እነዚህ ሐይቆች የስምጥ ሸለቆ ሐይቆች፣ በእሳተ ጎሞራ ፍንዳታ የተፈጠሩ ሐይቆች እና ተራራማ ሐይቆች በሚል በሦስት ምድብ ይታወቃሉ።

እነዚህ የሀገራችን ሐይቆች የቱሪዝም መዳረሻ እንዲሆኑ ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር የገንዘብ ሚኒስቴር በጉምሩክ አዋጅ ቁጥር 859/2006 (እንደተሻሻለ) አንቀጽ 129 በተሰጠው ሥልጣን መሠረት፤ በንግድ ሥራ ላይ የተሠማሩ ሰዎች በሞተር ኃይል የሚሠሩ የተለያዩ ዓይነት ጀልባዎችን ለአንድ ዓመት ያህል ከማናቸውም ቀረጥ እና ታክስ ነጻ ሆነው ወደ ሀገር ውስጥ እንዲያስገቡ የሚያስችል መመሪያ መስከረም 3 ቀን 2018 ማውጣቱ ይታወሳል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ