መስከረም 20/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) አቢሲንያ ባንክ በዛሬው ዕለት ዓመታዊ የባለአክስዮኖች 29ኛ መደበኛ እና 16ኛ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤው አካሂዷል።

በጉባኤው ላይ እ.ኤ.አ በ2024/25 ወይም በ2017 ዓ.ም የሒሳብ ዓመት ሪፖርት የቀረበ ሲሆን፤ የባንኩ አጠቃላይ ሀብት 286 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር መድረሱን አስታውቋል፡፡

ይህም ካለፈው ዓመት አጠቃላይ ሀብት ማለትም ከ222 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ጋር ሲነጻጸር የ63 ነጥብ 9 ቢሊዮን ወይም የ28 ነጥብ 8 በመቶ ዕድገት ማሳየቱን የአቢሲኒያ ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር አቶ መኮንን ማንያዘዋል ገልጸዋል።

Post image

ባለፈው የሒሳብ ዓመት የባንኩ ጠቅላላ ገቢው 39 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር መድረሱን የገለጹ ሲሆን፤ ውጤቱ ካለፈው ተመሳሳይ ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ11 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ዕድገት አሳይቷል ብለዋል።

ከጠቅላላ ገቢው ውስጥም ከብድር ወለድ የተገኘው ገቢ ከፍተኛውን ድርሻ እንደሚይዝ አክለዋል።

ጠቅላላ ወጪውን በሚመለከተም 29 ቢሊዮን ብር መሆኑን የገለጹት ሊቀመንበሩ፤ ካለፈው ተመሳሳይ የሒሳብ ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ6 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ወይም የ28 ነጥብ 9 በመቶ ዕድገት እንዳለው ተናግረዋል።

ለአጠቃላይ ወጪው መጨመርም በዋናነት ለተቀማጭ ገንዘብ የተከፈለው ወለድ 35 ነጥብ 6 በመቶ በመያዝ ከፍተኛ ድርሻ ያለው ሲሆን፤ ለሠራተኞች የተከፈለው ደመወዝና ጥቅማጥቅም 33 ነጥብ 7 በመቶ እንዲሁም ለጠቅላላና አስተዳደራዊ ወጪዎች 21ነጥብ 5 በመቶ እና የመጠባበቂያ ተቀናሽ ደግሞ የ 9 ነጥብ 1 በመቶ ድርሻ እንደሚይዝ ገልጸዋል።

Post image

በተጨማሪም ባንኩ በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት ለመንግሥት መከፈል ያለበት የትርፍ ግብር ከተቀነሰ በኋላ፤ ከ7 ቢሊዮን 298 ሚሊዮን 505 ሺሕ ብር በላይ የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታውቀዋል፡፡

አጠቃላይ ካፒታሉም ወደ 28 መጥብ 8 ቢሊዮን ብር ከፍ ማለቱን ገልጸው፤ የተከፈለ የካፒታል መጠኑ ደግሞ ባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከተመዘገበው ከብር ከ14 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር 15 ቢሊዮን ብር ማደጉን ተናግረዋል።

በ2017 የሒሳብ ዓመት ባንኩ አዲስ የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ ቀርጾ ወደ ሥራ መግባቱን የገለጹት ሊቀመንበሩ፤ ባለፈው የስትራቴጂክ ዘመን ላይ የታዩ መልካም የሥራ አፈፃፀሞችን አጠናክሮ በመቀጠል፣ ድክመቶችና ስጋቶችን በመለየትና መፍትሔ በማስቀመጥ በአምስት ዓመቱ ስትራቴጂክ ዕቅድ የተቀመጡ ግቦችን ለማሳካት ከፍተኛ ጥረት ይደረጋል ብለዋል።

አክለውም ባንኩ ተለዋዋጭ በሆነ የንግድ ሥርዓት ውስጥ ብቁና ተወዳዳሪ ሆኖ ለመገኘት የሚያስችሉትን አዳዲስ አሠራሮች አካትቶ በመጓዝ የታሰበውን የዕድገት ግብ ለማሳካት እና የባለአክሲዮኖችን የትርፍ ክፍፍል ድርሻ ከፍ ለማድረግ አጠናክሮ እንደሚሰራ አስታውቀዋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ