ሰኔ 24/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የእናቶችና ሕጻናት ሞት እና የሞት መንስኤዎችን ለመለየት እና ክትትል ለማድረግ የሚያስችል የናሙና ምዝገባ ስርዓት (Sample registration system) የመግባቢያ ስምምነት ከክልል የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩቶች ጋር ተፈራርሟል።
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መሳይ ሀይሉ ለአሐዱ እንደገለጹት፤ ኢንስቲትዩቱ የናሙና ምዝገባ ሥርዓቱን ለማስጀመር ቅድመ ዝግጅት ሲያደርግ የቆየ ሲሆን፤ ዓላማው በኢትዮጵያ የእናቶችና ሕጻናት ሞት እና የሞት መንስኤዎችን እንዲሁም አጠቃላይ የበሽታ ስርጭት መለየት እና ያሉትን የክትትል ስርዓቶች ማጠናከር ነው።
ጥናት እና ክትትሉ በሀገር አቀፍ ደረጃ በሁሉም ክልልሎች በተመረጡ ወረዳዎች እና ቀበሌዎች እንዲከናወን ለማድረግ ከክልል ጤና ቢሮ ጋር በመተባበር ተግባራዊ ይሆናል ተብሏል፡፡
ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ውስጥ በኢትዮጵያ የእናቶች እና ሕጻናት ሞት አሁንም በአሳሳቢ ደረጃ ላይ እንዳለ ጥናቶች እንደሚያሳዩ ተገልጿል።
የኢንስቲትዩቱ የብሔራዊ የጤና መርጃ አስተዳደር ቅመራና ትንተና ማዕከል ከክልል ጤና ቢሮና ከሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር የእናቶችና ሕጻናት የሞት መንስኤዎችን መረጃ ለማሰባሰብ ለውሳኔ ሰጪ አካላት ማስረጃ ለማቅረብ የሚያስችል የክትትልና ጥናት ማስጀመሪያ መሆኑም ተመላክቷል።
የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ውስጥ የሚገኘው የብሔራዊ መረጃ አስተዳደር ቅመራና እና ትንተና ማዕከል፤ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ መረጃዎችን በመጠቀም ለሀገር አቀፍ ጤና አገልግሎት ግብዓት የሚሆኑ ማስረጃዎችን በመመርመር ሲያቀርብ መቆየቱ ተነግሯል፡፡
ነግር ግን አብዛኛዎቹ የመረጃ ምንጮች ሙሉነት እና ወጥነት ስለሚጎድላቸው፤ ስምምነቱ የናሙና ምዝገባ ስርዓትን በመዘርጋት የመረጃ ክፍተቶችን በመሙላት በሀገሪቷ ያለውን የጤና ልማት እና ኢንቨስትመንት በማስረጃ የተደገፈ ውሳኔዎችን ለማሳለጥ የሚረዳ መሆኑም ተገልጿል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
ኢንስቲትዩቱ የእናቶችና ሕጻናት ሞት እና የሞት መንስኤዎችን ለመለየት እና ክትትል ለማድረግ የሚያስችል የናሙና ምዝገባ ስርዓት የማስጀመሪያ ሥምምነት ተፈራረመ
