ሰኔ 24/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት የአገልግሎት ንግድን ሳይጨምር ለዓለም ገበያ ካቀረበቻቸው ሸቀጦች ያገኘችው የውጭ ምንዛሪ ነዳጅ እና የፍጆታ እቃዎች ከሸመተችበት ያነሰ በመሆኑ፤ የንግድ መዛባት ለማስተካከል አስቻይ አለማድረጉን የምጣኔ ሀብት ባለሞያዎች ለአሐዱ አስታውቀዋል።
በአሁን ሰዓት እየታየ ያለውን በአጠቃላይ የንግድ ሚዛን መዛባትን ለማስተካከል፤ የኢትዮጵያ መንግሥት 'ሊወሰዱ ይገባል' ከሚላቸው እርምጃዎች መካከል አንዱ፤ ለነዳጅ እና የፍጆታ እቃዎች ሀገሪቷ የምታወጣው የውጭ ምንዛሪ መቀነስ እንደሆነ የሚያስረዱት የምጣኔ ሐብት ባለሞያው እንዳይላሉ ሰለሞን ናቸው።
"የተዛባውን የንግድ ሚዛን ማረቅ ከመንግሥት የገንዘብ እና የወጪ ንግድ ፖሊሲ ጭምር ጋር የተቆራኘ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ መዋቅራዊ ችግሮች መፍታት የሚጠይቅ ሥራ መታከል አለበት" ሲሉ ለአሐዱ ገልጸዋል።
በዜጎች ላይ ጫና እያሳደረ የሚገኘው የኑሮ ውድነት መባባስ ምክንያት ውስጥ፤ መንግሥት ከውጭ ለሚገቡ የነዳጅ እና የፍጆታ እቃዎች የሚያወጣው ወጪ አንዱ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ፤ መንግሥት የነዳጅ ድጎማ ሲያቆም የነዳጅ ምርቶች የመሸጫ ዋጋ ከታክስ ጋር ተደምሮ ወደ ሸማቾች እንደሚሸጋገር ጠቁመው፤ በመሆኑም የዋጋ መጨመር እና መቀነስ በዓለም አቀፍ ገበያ ላይ የነዳጅ ዋጋ መቀነስ ጋር የተቆራኘ እንደሆነ አንስተዋል፡፡ "ይህም ከኢትዮጵያ ቁጥጥር ውጪ ነው" ሲሉ አስረድተዋል።
የኢንቨስትመንት እና የፋይናንስ አማካሪው ከፈለኝ ሀይሉ በበኩላቸው፤ "ከሚወጡ የውጭ ምንዛሬ በተጨማሪ ታክስ መጨመር እና ሌሎች አካሄዶች ዜጎች ላይ ጫና እያሳደረ ነው" ብለዋል፡፡
አክለውም፤ ይሄ አካሄድ መሠረታዊ ስህተት እንደሆነ እና የችግሮች መፍቻ መንገድ እንደማይሆን ጠቁመዋል።
ወደ ውጭ ገበያ በሚላኩ እቃዎች ሳቢያ በቂ የዶላር ገቢ አለመኖር ተጠቃሽ መሆኑን ገልጸው፤ የታክስ መብዛት ምክንያቶች የመንግሥት ወጪዎች መጨመር እና የበጀት ጉድለትን መሙላት እንደሆነ አስገንዝበዋል።
"መንግሥት ከውጪ በሚሸምተው ሸቀጥ ላይ ጥገኛ በሆነ ኢኮኖሚ ውስጥ የመገበያያ ገንዘቡ የበለጠ እየተዳከመ የመሄድ ዕድል ካለው፤ ዋጋ ላይ የሚያመጣው ልዩነት የዚያኑ ያክል ነው" የሚሉት የኢኮኖሚ ባለሞያዎች፤ በዚህ ምክንያት ከሸማቾች አኳያ የዋጋ ጭማሪ ሊኖር እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
መንግሥት ለነዳጅ እና ለፍጆታ እቃዎች የሚያወጣው የውጭ ምንዛሬ የንግድ ሥርዓቱ እንዲዛባ ምክንያት ሆኗል ተባለ
