ሰኔ 24/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለአስርት ዓመታት ያስቆጠረውና አሜሪካ በሶሪያ ላይ የጣለችውን ማዕቀብ ሙሉ ለሙሉ እንደሚያነሱ የገለጹ ሲሆን፤ የቀድሞውን የበሽር አላሳድ መንግሥት የገረሰሱት የሃያት ታህሪር አልሻም ታጣቂዎች ጥምረት መሪ አህመድ አል ሻራ የአሸባሪነት ስያሜያቸው እንዲገመገምላቸው ትዕዛዝ አስተላልፈዋል።
ትራምፕ በአውሮፕያኑ ባለፈው ዓመት መጨረሻ ላይ የሃያት ታህሪር አል ሻም (ኤች.ቲ.ኤስ) እና ሌሎች ታጣቂ ቡድኖች የቀድሞውን የበሽር አላሳድ መንግሥትን ከገረሰሱ ወዲህ፤ በሶሪያ ላይ አሜሪካ የጣለችውን ማዕቀብ ለማንሳት በትላንትናው እለት ፊርማቸውን አኑረዋል፡፡
"አሜሪካ የውጭ አሸባሪ ድርጅቶች ብላ በፈረጀቻቸው ላይ የጣለችው ማዕቀብም እንዳለ ይቆያል" ያሉት ትራምፕ፤ ሆኖም የኤች.ቲ.ኤስን ስያሜ እንዲሁም የአል-ሻራ መለያን በተለይ መልኩ የተነደፈ "ዓለም አቀፍ አሸባሪ" የሚል መለያ ወይንም ስያሜ እንዲገመግም ለውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ ማርኮ ሩቢዮ መመሪያ መስጠታቸውን አር ቲ ዘግቧል።
ዋሽንግተን በአውሮጵያኑ 1979 ለመጀመሪያ ጊዜ ሶሪያን የሽብርተኝነት መንግሥት ስትል መፈረጇ የሚታወቅ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት ደግሞ ለሶሪያ ጊዜያዊ መንግሥትን ድጋፍ በማድረግ እውቅና ሰጥተዋለች፡፡
ውሳኔው የመጣው ትራምፕ ከአዲሱ የሶሪያ ፕሬዝዳን አህመድ አል ሻራ ጋር በሪያድ ያደረጉትን ውይይት ተከትሎ ሲሆን፤ ውይይቱም በሶሪያ መልሶ ግንባታ እና ከእስራኤል ጋር ያላትን ግንኙነት ወደ መደበኛ ማድረግ ላይ ያተኮረ ነው። በወቅቱ ትራምፕ በደማስቆ ለሚገኘው አዲሱ አመራር የታላቅነትና ዕውቅና ለመስጠት ከወራት በፊት ቃል መግባታቸው ይታወሳል።
ዋሽንግተንን ከደማስቆ ጋር ያላትን ግንኙነት ለማስቀጠል በቱርክ የአሜሪካ አምባሳደር የነበሩትና ለረጅም ጊዜ የትራምፕ ታማኝ የነበሩትን ቶማስ ባራክን የአሜሪካ የሶሪያ ልዩ መልዕክተኛ ተደርገው ተሾመዋል፡፡
ባራክን በትላንትናው ዕለት ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፤ በሶሪያ የፖለቲካ ለውጥ እና በአሜሪካ የነፃነት የመጀመሪያዎቹ ዓመታት መካከል ያለውን ታሪካዊ ግንኙነት መቀጠሉን ጠቁመዋል፡፡
የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ከዚህ ቀደም፤ "ሶሪያ አይ.ኤስ.አይ.ኤስን እና ሌሎችን ጨምሮ የጂሃዲስት ቡድኖች መጫወቻ ሜዳ ሆና ቆይታለች" ሲሉ ተናግረው እንደነበር ይታወሳል፡፡
"ነገር ግን ይህ የሶሪያን ሕዝብ ዋጋ አስከፍሎ የቆየ ነው" ያሉት ሩብዮ፤ በአዲሱ ጊዜያዊ መንግሥት ይቆማል ብለው እንደሚያምኑም ተናግረዋል፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
ዶናልድ ትራምፕ የሶሪያው መሪ የአሸባሪነት ስያሜ እንዲገመገም አዘዙ
ፕሬዝዳንቱ አሜሪካ በሶሪያ ላይ የጣለችው ማዕቀብ እንዲነሳ ፈርመዋል
