መስከረም 26/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) ሁለተኛው ዓለም አቀፍ የጤና እንክብካቤ ኮንፈረንስ "በ21ኛው ክፍለ ዘመን የመጀመሪያ ደረጃ የጤና እንክብካቤን ማሳደግ እና ሰውን ማስቀደም" በሚል መሪ ቃል ከ64 በላይ ሀገራት የተውጣጡ ተሳታፊዎች በተገኙበት በአዲስ አበባ በዓድዋ ሙዚየም በመካሄድ ላይ ይገኛል።
በኮንፍረንሱ ገለጻ ያደረጉት የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ፤ ኢትዮጵያ ባለፉት 20 ዓመታት የዜጎችን ጤና የሚያሻሽሉ ሥራዎችን ተግባራዊ ስታደርግ መቆየቷን ጠቁመው፤ በዚህም በዓለም አቀፍ ደረጃ የተሻለ ደረጃ ላይ እንድትሆን ማስቻሉን አብራርተዋል።

በዚህም ሂደት የእናቶችን የወሊድ ሞት ምጣኔ በመቀነስ እና የጤና ተቋማት ተደራሽነትን በማስፋፋት ሥራ የመጀመሪያ ደረጃ ጤና ክብካቤ አስተዋጽኦ የጎላ ስለመሆኑ ጠቁመዋል።
ከአጋር እና ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን የሕብረተሰቡን ፍትሐዊ የጤና ተጠቃሚነት ለማስፋትም የተለያዩ ለውጦች መተግበራቸው ይቀጥላል ነው ያሉት።
የመጀመሪያ ደረጃ ጤና ክብካቤ በጤናው ዘርፍ ብቻ ሳይሆን የመንግሥት የልማት ግብ አጀንዳ ተደርጎ እየተሠራበት ይገኛል ሲሉም ገልጸዋል።
የእናቶችና ሕጻናት ሞት ቅነሳ እንዲሁም በበሽታ ቅድመ መከላከል በኩል ለውጥ መምጣቱን ገልጸው፤ በጤና ኢንቨስትመንት ትኩረት የተሰጠው የመሰረተ ልማት ግንባታም እየተስፋፋ መሆኑን ተናግረዋል።

የዓለም አቀፉ የመጀመሪያ ደረጃ ጤና ክብካቤ በኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አብነት ዘለቀ በበኩላቸው፤ ባለፉት ዓመታት በኢትዮጵያ የመጀመሪያ ደረጃ ጤና ክብካቤን ለማኅበረሰቡ ተደራሽ ለማድረግ ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመቀናጀት ሲተገበር መቆየቱን አብራርተዋል።
በዚህም በመረጃ ላይ የተመሠረተ የጤና ሥርዓትን መገንባት፣ የውስጥ ፖሊሲዎችን ማሻሻል፣ የጤና ባለሙያዎችን አቅም ማጎልበት እና ማኅበረሰብ ተኮር የጤና ተደራሽነትን ማስፋት ላይ ውጤታማ ሥራ መሥራት ተችሏል ብለዋል።
ኮንፈረንሱ ከሃሳብ ልውውጥ የተሻገረ አጋርነትን በመመሥረት ዘላቂ የጤና ክብካቤን ለመተግበር መንቀሳቀስ ይገባልም ሲሉ አሳስበዋል።
ሀገራት የጤና ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የመጀመሪያ ደረጃ የማኅበረሰብ ጤና ክብካቤ ላይ ትኩረት አድርገው መሥራት እንደሚጠበቅባቸውም በመድረኩ ተመላክቷል።
በኮንፈረንሱ ከተለያዩ ሀገራት የተውጣጡ ከ705 በላይ ተሳታፊዎች የተገኙ ሲሆን፤ ለተከታታይ አምስት ቀናት በተለያዩ ሁነቶች የሚቀጥል ይሆናል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ