መስከረም 26/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለተለያዩ ችግሮች ተጋላጭ ለሆኑ ዜጎች፤ ከ28 ሺሕ ኪሎ ግራም በላይ የሚመዝን የቁሳቁስ ድጋፍ ለሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በዛሬው ዕለት አስረክቧል።

በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ሁሪያ አሊ፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለሀገር ኢኮኖሚ ከሚያበረክተው አስተዋጽኦ ባሻገር፤ ማህበራዊ ኃላፊነትን በመወጣት ትብብርን (አብሮነትን) የሚያጎለብቱ ሥራዎችን በመስራት ላይ ይገኛል ሲሉ በርክክቡ ወቅት ተናግረዋል።

Post image

የተደረገው የቁሳቁስ ድጋፍ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ለሚገኙና በተለያዩ ችግሮች ምክንያት ድጋፍ የሚሹ የማህበረሰብ ክፍሎችን ለመደረስ ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር አንስተዋል።

ድጋፉም አልባሳትን ጨምሮ የተለያዩ ቁሳቁስ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታዋ፤ በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል በተለይ ድጋፍ ለሚሹ ሕጻናት፣ እናቶችና ለችግር ለተጋለጡ ተደራሽ እንደሚደረግ ተናግረዋል።

በዚህም የኢትዮጵያ አየር መንገድ አጋርነቱን ያሳየበት እና ማህበራዊ ኃላፊነትን ከመወጣት አንጻርም ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው ብለዋል።

እንዲሁም ለአንድ ሀገር የኢኮሚያዊ እድገት ለማምጣት ትብብር እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ