መስከረም 26/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) ‎6ኛው የኢፌዲሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና የፌዴሬሽን ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን መክፈቻ ሥነ-ሥርዓት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በተገኙበት በዛሬው ዕለት ተካሂዷል።

በዚህም የሥራ ዘመን መክፈቻ ሥነ-ሥርዓቱ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ፤ የፌደራል መንግሥቱን ዓመታዊ ዝርዝር ዕቅድ አቅርበዋል።

በዚህም የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በ2017 በጀት ዓመት 8 ነጥብ 8 በመቶ እድገት ማስመዝገቡን ገልጸው፤ በተያዘው በጀት ዓመት 9 በመቶ የኢኮኖሚ ዕድገት ለማረጋገጥ ይሰራል ብለዋል።

ፕሬዝደንቱ አክለውም በ2016 በጀት ዓመት በግብርና ዘርፍ 1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ኩንታል መመረቱ በማስታወስ፤ በ2017 በጀት ዓመት የተመረተው 1 ነጥብ 57 ቢሊዮን ኩንታል ከቀደመው በጀት ዓመት ጋር ሲነጻጸር 24 ነጥብ 7 በመቶ ብልጫ እንዳለው አስረድተዋል፡፡

የኢንደስትሪዎች የማምረት አቅም ከ59 ወደ 65 በመቶ ማደጉን አያይዘው የገለጹት ፕሬዝዳንቱ፤ በተጨማሪም የሲሚንቶ ምርት ወደ 9 ነጥብ 1 በመቶ መጨመሩን ተናግረዋል፡፡

በ2016 በጀት ዓመት ከነበረው 7 ነጥብ 5 ሚሊየን ቶን የሲሚንቶ ምርት በ2017 በጀት ዓመት ወደ 9 ነጥብ 1 ሚሊዮን ቶን እንዲጨምር ማድረግ ስለመቻሉም አስረድተዋል፡፡

በባለፈው ዓመት ዝቅተኛ ገቢያ ያላቸው ተማሪዎች ምገባ በማከናወን ከትምህርታቸው እንደይቀሩ ተሰርቷል ብለዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ከአካታችት አኳያ ጥረት በመደረጉ፤ በበጀት ዓመቱ ዘመናዊ ለአይነ ስውራን ዜጎች ትምህርት ቤቶች እንዲገነቡ መደረጉን በአብነት አውስተዋል፡፡

በ2018 በጀት ዓመት 9 በመቶ የሀገር ውስጥ የምርት እድገት ለማረጋገጥ በተያዘው እቅድ፤ ምርትን በአይነት እና በጥረት እንደሚያሳድግ የገለጹም ሲሆን፤ ለአብነትም የግሉ ዘርፍ ተሳታፊነትን ማጠናከር ላይ እንደሚሰራ አንስተዋል፡፡

በተጨማሪም ምርታማነት ጥራት ባለው መልኩ በመጨመር፤ ተወዳዳሪ የሆነ የወጪ ንግድ እንቅስቃሴ እንዲኖር እንደሚሰራ ጠቁመዋል።

እንዲሁም የዋጋ ግሽበት ወደ ነጠላ አኃዝ እንዲወርድና የዜጎችን የኑሮ ጫና ለማቃለል እንደሚሰራ ገልጸዋል።

የሥራ ዕድል መፍጠር የመንግሥት ቀዳሚ ሚና መሆኑን የገለጹት ፕሬዚዳንት ታዬ፤ ይህንንም ለማሳካት በሀገር ውስጥና ውጪ የሥራ አማራጮችን እንደሚፈጠሩ ገልጸዋል።

ግብርናው ከባህላዊ አመራረት በማላቀቅ በቴክኖሎጂና ፋይናንስ በመደገፍ 6 ነጥብ 8 በመቶ ዕድገት ለማስመዝገብ መታቀዱንም አንስተዋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ