ጥቅምት 6/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) ኢትዮ ቴሌኮም አካታች የዲጂታል ትራንስፎርሜሽንን ለማፋጠን የሚያስችሉና በክላውድ ላይ የተመሰረቱ 'ዘ ኔክሰስ ስማርት ዲቫይስ' እና 'ክላውድ ዎርክ ስፔስ' መተግበሪያዎችን በዛሬው ዕለት አስተዋውቋል።
ኩባንያው የቀጣዩ አድማሱን በማስፋት፤ የዲጂታልን ትስስርን በሁሉም ዘርፍ ከማሳደግ ባሻገር እስከ አውሮጵያኑ 2028 ድረስ በስትራቴጂ ንድፍ ሃሳብ፣ በቴክኖሎጂ ፈጠራ፣ በማኑፋክቸሪንግ እና በሥነ-ምህዳር አጋርነት እንደሚሰራ ገልጿል።
ይህ የዲጂታል ቴክኖሎጅ መተግበሪያ፤ በሁሉም የኢትዮጵያ ክፍሎች የሚገኙ ደንበኞችን ወደ አንድ በማስተሳሰር፤ የዲጂታል ግብይትን ለመፈፀም እንደሚረዳ የኩባንያዉ ፍሬህይወት ታምሩ ተናግረዋል።

ዋና ሥራ አስፈፃሚዋ ላለፉት ስድስት ዓመታት የኢትዮጵያን ዲጅታል ጉዞ እውን ለማድረግ፤ በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች የመሰረተ ልማት ግንባታ ሲከናወን ቆይቷል ብለዋል።
በዚህም በየዘርፉ ስኬታማ ለመሆን የቀጣይ የኢትዮጵያ የዲጂታል ጉዞ ሊያሳካ የሚችለውን 'ዘ ኒክሰስ' በክላውድ ላይ የተመሰረቱ ስማርት መሳሪያዎች ለሁሉም ደንበኞች ተደራሽ ማድረግ የሚያስችል መተግበሪያ ኩባንያው አስጀምሯል ብለዋል።
ይህ የቴክኖሎጂ መተግበሪያ ደንበኞች፣ በስማርት ስልክ፣ በታብሌትና የተለያዩ የእጅ ስልኮችን በመጠቀም፤ የገበያ ትስስርን በመፍጠር ግብይታቸውን የሚያፋጥንላቸው ነው ሲሉ የኩባንያዉ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ገልጸዋል።
ዘኔክሰስ ኢንተርኔት ተጠቃሚነትን በማሳደግ፤ ግብይቱን፣ ግብርናውን፣ ትምህርቱን እና ሌሎችንም ሥራዎች ስለመሆኑም ተናግረዋል፡፡

መተግበሪያው አካታችነትን እና ዕድሎችን በማስፋት የዲጂታል ተደራሽነትን እና የቴክኖሎጂ ፈጠራን ለማፋጠን ያለው ጠቀሜታ የላቀ እንደሆነም አስረድተዋል።
በተጨማሪም የክላውድ ወርክስፔስ መፍትሔ ቢዝነሶችን፣ የመንግሥት እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን ቨርቹዋል ዴስክቶፖችን እና አፕሊኬሽኖችን ከማንኛውም መተግበሪያ ጋር ለማገናኘት የሚያስችል ሲሆን፤ ይህም የአይ.ቲ ወጪዎችን በመቀነስ ምርታማነትን ለማሳደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው ብለዋል።
ኢትዮ ቴሌኮም ካለፉት ስድስት ዓመታት ጀምሮ የቀጣይ ዲጂታል ኢትዮጵያን ወደ አንድ ለማምጣት የዕለት ተእለት እንቅስቃሴዎችን ትኩረት በመስጠት የተለያዩ ቴክኖሎጂችን እያስተዋወቀ እንደሚገኝ አስታውቋል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ