ሕዳር 25/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) በየቀኑ እስከ 60 ሺሕ ዜጎችን የሚያስተናግደው የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት፤ በዋና ዋና የትኬት መቁረጫ ጣቢያዎች ላይ የሚስተዋለውን የሰልፍ ብዛት ለመቀነስ የሚያስችል አዲስ የክፍያ ሥርዓት መዘርጋቱን ይፋ አድርጓል።

አሁን ላይ በአራቱ የመነሻ ጣቢያዎችና ስቴዲየምን ጨምሮ በአምስት ቦታዎች ላይ የባቡር ትኬት በቴሌ ብር አማካይነት መቁረጥ መጀመሩን የገለጹት፤ የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ብርሃኑ አበባው (ዶ/ር) ናቸው።

ተጓዦች በሞባይል ስልካቸው በቴሌ ብር ትኬት በመቁረጥ የሚሰጣቸውን ደረሰኝ ለሠራተኞች በማሳየት፤ በቀላሉ ወደ ባቡር መግባት የሚችሉበት ሥርዓት ተግባራዊ መሆኑ ተገልጿል።

Post image

ድርጅቱ በየዕለቱ ከ55 ሺሕ እስከ 60 ሺሕ የሚደርሱ ዜጎችን የሚያመላልስ ሲሆን፤ በተለይም በሥራ መግቢያና መውጫ ሰዓታት የተጠቃሚዎች ቁጥር በእጅጉ ከፍ ይላል። ይህም የትኬት መቁረጫ ጣቢያዎች ላይ ረጃጅም ሰልፎች እንዲስተዋሉ ምክንያት ሆኗል። ዋና ሥራ አስፈጻሚው ይህንን የሰልፍ ችግር ለመቅረፍ በቴሌ ብር የመክፈያ ሥርዓት መጀመሩ ትልቅ እገዛ ያደርጋል ብለዋል።

"ከተጠቃሚው ብዛት አንጻር በተለይም ጠዋት እና ማታ የትኬት መቁረጫ ጣቢያዎች ላይ ረጃጅም ሰልፎች ይታያሉ። ይህን ለማስቀረት እንዲያግዝ በቴሌ ብር ትኬታቸውን በአራቱም መነሻ ጣቢያዎች እንዲሁም ስቴዲየም በሚገኙ የትኬት መሸጫዎች ቆርጠው በስልካቸው ደረሰኝ በማሳየት ማለፍ ይችላሉ” በማለት አዲሱን ሥርዓት አብራርተዋል።

ይህ የክፍያ ሥርዓት የተዘረጋው ትኬት መቁረጥ በሚቻልባቸው አምስት ቦታዎች ላይ ሲሆን፤ አራቱ የመነሻና መድረሻ ጣቢያዎች ሲሆኑ፣ አምስተኛው ደግሞ ስቴዲየም ጣቢያ ነው።

ዋና ሥራ አስፈጻሚው የባቡር ትራንስፖርት ተጠቃሚዎች ቁጥር ከፍተኛ መሆኑን የገለጹ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት 19 ባቡሮች ብቻ አገልግሎት እየሰጡ መሆናቸውን ጠቁመዋል። ይህ ቁጥር ከተጠቃሚዎች ብዛት አንጻር በቂ እንዳልሆነ በማንሳትም፤ የባቡሮችን ቁጥር ለማሳደግና በተለያዩ ብልሽቶች ምክንያት ቆመው የሚገኙ ባቡሮች ተጠግነው ወደ አገልግሎት እንዲገቡ የማድረግ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር አገልግሎት ከ10 ዓመታት በፊት ሥራ ሲጀምር 41 ባቡሮችን ይዞ እንደነበር የሚታወስ ሲሆን፤ አሁን ላይ 21 ባቡሮች በብልሽት ምክንያት ቆመው እንደሚገኙ መረጃዎች ያሳያሉ።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ