መስከረም 28/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) 24 ሰዓት ያለማቋረጥ ጨረር የሚያመነጩ የጨረራና የኑክሌር ቁሶች መኖራቸውን እና ቁጥጥር ሳይደረግባቸውና ዕውቅና ሳይሰጣቸው የተሰራጩ ምንም አይነት የጨረራና ኑክሌር መሳሪያዎች አለመኖራቸውን የኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ባለስልጣን አስታውቋል።
ኢትዮጵያም ሕክምናን ጨምሮ ለተለያዩ አገልግሎቶች የጨረራ አገልግሎትን ጥቅም ላይ እያዋለች መሆኑ ይታወቃል፡፡
የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የጨረራ እና ኑክሌር ቴክኖሎጂ ቁጥጥር ሕግ ማስፈፀም ቡድን መሪ ሥራ አስፈፃሚ አቶ እሸቱ ጥላሁን ከአሐዱ ሁሉ ደህና ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ መሳሪያዎች ወደሀገር ውስጥ ሲገቡ ጥብቅ ቁጥጥር እንደሚደረግባቸው አንስተው ከገቡ በኋላም ለመጠቀም የሚያስችለውን መስፈርት ካሟሉ እና የተግባር ፈቃድ ከተሰጣቸው በኋላ አገልግሎት ላይ እንደሚውሉ ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ ውስጥ ለተለያየ አገልግሎት ጥቅም ላይ የሚውሉ ከ3 ሺሕ በላይ የጨረራ አመንጪ መሳሪያዎች እንደሚገኙም የኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ባለስልጣን አስታውቋል።
እነዚህም ጀነሬተሮችን እና የሬዲዮ ሥርጭቶችን ጨምሮ ለበርካታ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎቶች ጥቅም ላይ የሚውሉ መሆናቸውን የጠቆሙት መሪ ሥራ አስፈፃሚው፤ እነዚህ መሳሪያዎችም በጨረራና ኑክሌር ቴክኖሎጂ አዋጅ 1025/2009 መሰረት ስለሚገባው መሳሪያ ምንነት፣ ለምን አላማ እንደሆነ፣ በማን እንደሆነና ስለ ጥራቱና ደረጃው እንዲሁም አጠቃላይ ዝርዝር መረጃ በስፋት እንደሚመዘገብ ገልጸዋል።
ከኤሌክትሪክ ጋር ብቻ ሲገናኙ ጨረር ማመንጨት የሚችሉ እንደ 'ኤክስ-ሬይ' እና 'ሲቲ ስካን' የመሳሰሉ መሳሪያዎች እንዲሁም በተለያየ አጋጣሚ ለማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ጥቅም ላይ የሚውሉ መሆናቸውን ገልጸው፤ ለአብነትም ለጤና፣ ግብርና፣ ለምርምር እና ኢንዱስትሪዎች ላይ በስፋት አገልግሎት እንደሚሰጡ አብራርተዋል።
ቡድን መሪው በማብራሪያቸው፤ ከ6 ወር እስከ 2 ዓመት እንደ ማሽኖቹ ባህሪ እና አገልግሎት እየታየ በማሕብረተሰቡ ላይ ጉዳት እንደማያስከትሉ ለማረጋገጥ ቁጥጥር እንደሚደረግ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በፈረመቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች መሰረት ተቋሙ በኢትዮጵያ ውስጥ ስለሚገኙ የጨረራና ኑክሌር መሳሪያዎች አድራሻ እንደሚያውቅ እና ቁጥጥር እና ክትትል እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡
ማንኛውም ግለሰብ ወይም ድርጅት የጨረራና ኑክሌር አመንጪ ቁሶችን ወደ ሀገር ውስጥ ከማስገባቱ በፊት፤ ለምን አገልግሎት እንደሚውል የማሳወቅ ቅዴታ እንደተጣለበትም አብራርተዋል።
የተቋሙን ይሁንታ ሳያገኙ ከተለያዩ ጎረቤት ሀገራት የሚገቡትን አንዳንድ መሳሪያዎች ከፌዴሬል ፖሊስና ሌሎች ከባለድርሻዎች ጋር በመተባበር ክትትል ይደረግባቸዋል ተብሏል፡፡
ጨረራ ወይም ራዲየሽን (Radiation) የሚለው ቃል በቀላሉ ሲገለፅ፤ አቅም ወይም ኢነርጂ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ በሞገድ ወይም በቅንጣት መልክ ሲጓጓዝ ማለት ሲሆን፤
ጨረራ ወይም ራዲየሽን (Radiation) በሞገድ መልክ ወይም በአነስተኛ ልዩ ልዩ ቅንጣቶችአቅም ወይም ኢነርጂ ከቦታ ወደ ቦታ የሚጓዝ ኃይል ሲሆን፤ የጨረራ ዓይነቶች በዋነኝነት "አዮን ፈጣሪ ጨረራ" እና "አዮን የማይፈጥር ጨረራ" በመባል ይጠቀሳሉ።
በተለየ ከታወቁት የጨረራ ምንጮች መካከል ፀሐይ፣ በማብሰያ ክፍል ውስጥ ያሉ ማይክሮዌቭ ምድጃዎች እና በመኪና ውስጥ የምናዳምጣቸው ራዲዮዎች ይገኙበታል፡፡
ጨረራ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት እንዲሁም፤ በጤና እክል ምክንያት የሚመጡ የውስጥ አካል ችግሮችን፤ የካንሰር፤ የልብ በሽታን እና ሌሎች መሰል በሽዎችን ለመለየትና ለማከም ጨረራ በስፋት ጥቅም ላይ እየዋለ ይገኛል፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
ባለስልጣኑ እውቅና ሳይሰጣቸው የተሰራጩ ምንም አይነት የጨረራ አመንጪ መሳሪያዎች አለመኖራቸውን አስታወቀ
ኢትዮጵያ ውስጥ ከ3 ሺሕ በላይ የጨረራ አመንጪ መሳሪያዎች ይገኛሉ ተብሏል
