ጥቅምት 26/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) በተጠናቀቀው ሩብ ዓመት ማለትም ከሐምሌ 1 ቀን 2017 ዓ.ም እስከ መስከረም 30 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ፤ በ11ዱ ክፍለ ከተማዎች 1 ሺሕ 500 የደህንነት ካሜራዎች መግጠሙን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ለአሐዱ አስታውቋል።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኮማንደር ማርቆስ ታደሰ፤ ከተገጠሙት የደህንነት ካሜራዎች መካከል 160 የሚሆኑት በፖሊስ የዋና ማዘዣ ማዕከል ውስጥ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።

Post image

ኮማንደሩ ቴክኖሎጂን በማዘመን የደህንነት ካሜራዎች መግጠም ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ ያለበት ዋናኛ አላማ፤ በከተማዋ አስተማማኝ የሰላምና ደህንነትን ለማረጋገጥ፣ የትራፊክ አደጋን ለመቆጣጠር ሙስናና ብልሹ አሰራሮችን ለመቀነስ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

በተጨማሪም ከዚህ በፊት በከተማዋ በፀጥታው ዘርፍና በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ምክክር ለማድረግ ሲታሰብ አመራሮችንና አባላትን ከተለያዩ ቦታዎች በመጥራት በአንድ አዳራሽ ውስጥ ንግግር ሲደረግ እንደነበር ያስታወሱት ኮማንደር ማርቆስ፤ "ነገር ግን በአሁኑ ወቅት የትኛውም አመራር ይሁን አባል ባለበት ቦታ ሆኖ ለውይይት የሚቀርብበትን መንገድ የቴክኖሎጅ አሰራር በተያዘው ሦስት ወራት ውስጥ መዘርጋት ተችሏል" ብለዋል።

እንዲሁም አዲስ አበባ ከተማ የአፍሪካ ኅብረትን ጨምሮ የበርካታ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ተቋማት እና ዲፕሎማቶች መቀመጫ እንደመሆኗ፤ የተለያዩ ሀገራት መሪዎች ወደ ከተማዋ ሲገቡ የተሻለ ጥበቃንም ለማድረግ የየደህንነት ካሜራው እገዛ የጎላ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

Post image

የኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኮማንደር ማርቆስ አክለውም፤ ፖሊስ ጣቢዎቹ ለአገልግሎት ምቹ ከማድረግ ጎን ለጎን ዘመናዊ የመረጃ መቀበያ ስርዓት እና ወንጀልን ለመከላከል የሚያግዙ ልዩ ልዩ ቴክኖሎጂዎችን የማስገጠም ሥራን ለመስራት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ለአሐዱ ገልጸዋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ