በዓመት 3 ሚሊዮን የሚሆኑ ጉዳዮች በባህላዊ ፍርድ ቤት እንደሚታዩም የፍትህ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
በኢትዮጵያ የመሬት ጉዳይ ግጭት ከሚነሳባቸው ቀዳሚ ጉዳዮች አንዱ ነው። 43 በመቶ የሚሆኑት ግጭቶች እልባት የሚያገኙት በማኅበራዊ ፍትሕና በሽምግልና በመሳሰሉት መንገዶች ነው።
መንግሥት የፍትሕ ዘርፉ የሦስት ዓመት የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ይዞ እየሰራ ሲሆን፤ በዋናነት የባህላዊ ፍርድ ቤቶችን የማሳደግ ሥራ እየተከናወነ ይገኛል።
የኦሮሚያ ክልል ከ6 ሺሕ ቀበሌ በላይ የማኅበራዊ ሕግ ስርዓት እየተከተለና ግጭቶችን እየፈታ እንደሆነ ተነግሯል። በተመሳሳይ በሲዳማ ክልል ከ4 ሺሕ በላይ ቀበሌ ላይ ይህንን ሥራ በስፋት መስራት ችሏል።
በኦሮሚያ ክልል በቀበሌ ደረጃ የመጀመሪያ ደረጃ የባህል ፍርድ ቤቶች ሲቋቋሙ በወረዳ ደረጃ ደግሞ ይገባኝ ሰሚ የባህል ፍርድ ቤቶች መቋቋም መቻሉ ተገልጿል።
ይህ ባህላዊ ፍርድ ቤት በኦሮሞ እሴትና በገዳ ሥርዓት ላይ በመመስረት ይሰራል። በመሆኑም ለማኅበረሰቡ ባሕል መጎልበት ያለው አስተዋጽኦ ቀላል አይደለም። በኦሮሚያ ክልል የሚገኙ ባህላዊ ፍርድ ቤቶች በዓመት ከግማሽ ሚሊዮን በላይ የክስ መዝገቦችን ያስተናግዳሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በዓመት 3 ሚሊዮን ጉዳዮች በባህላዊ ፍርድ ቤት እንደሚታዩ የፍትሕ ሚኒስቴር ይገልጻል። 80 በመቶ የሚሆነው ኢትዮጵያዊም በባህላዊ ፍርዶች ቤቶች ላይ እምነት እንዳለው ይነሳል።
ባህላዊ ፍርድ ቤቶች ለሕብረተሰቡ ፍትሕን ከማፋጠን በተጨማሪ ለባህላዊ እሴቶች መጎልበት አስተዋጿቸው የላቀ መሆኑ ተጠቃሽ ነው።
በዛሬው ዕለትም ፍትሕ ሚኒስቴር "በኢትዮጵያ የመሠረተ ማኅበረሰብ ፍትሕ አጠቃላይ እይታ እና ወቅታዊ መረጃ" በሚል ከክልል ተቋማትና ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል።

የማኅበረሰብ ፍትሕን በማጠናከር ለሕብረተሰቡ የፍትሕ ጥያቄ ምላሽ መስጠት የሚያስችሉ አገልግሎቶች እየተተገበሩ መሆኑን የፍትሕ ሚኒስትር ዴኤታ ኤርሚያስ የማነብርሃን ገልጸዋል።
ከዚህ ቀደም ባህላዊ ፍርድ ቤቶች በሕግም ጭምር ተሽረው የቆዩ ነበሩ። ሕገ-መንግሥቱ ሲመሠረት ግን ለዚህ ፍርድ ቤት እውቅና መስጠቱን ሚኒስትር ዴኤታው አንስተዋል።

በተጨማሪም መንግሥት ባህል ውስጥ ገብቶ መመሪያ የመስጠት ሥራ አይሰራም ብለዋል። ዘመን የተሻገሩ ባህላዊ ስርዓቶችን እውቅና የመስጠት ሥራ እንደሚሰራ አስረድተዋል።
ሚኒስትር ዴኤታው ኤርሚያስ በኢትዮጵያ የመሠረተ የማኅበረሰብ ፍትሕን በማጠናከር ለሕብረተሰቡ የፍትሕ ጥያቄ ምላሽ መስጠት የሚያስችሉ አገልግሎቶች እየተተገበሩ መሆኑን ገልጸዋል።
ፍርድ ቤቶቹ በቤተሰብ አባላትና በማኅበረሰብ መካከል የሚፈጠሩ ማኅበራዊ ግጭቶችን በመፍታት ይረዳሉ። እርቅና ሰላምን ለማውረድና አንድነትን ለማጠናከር እንደሚረዱም ተመልክቷል። በዘመናዊ ፍርድ ቤቶች ትናንሽ ጉዳዮችን ለመዳኘት የሚያወጣውን ወጪ ስለሚቀንስም ጥቅሙ ከፍተኛ መሆኑ ይነሳል።
ባሕልን መሠረት ያደረገና እውነት ጎልቶ የሚወጣበት በመሆኑ ለዘመናዊ የፍትሕ ሥርዓትም እንደ ግብዓት እንደሚያገለግል ገልጸዋል። ከሰብዓዊ መብት አንጻር የሚነሱ ቅሬታዎችን ለመፍታት የአቅም ግንባታ ሥራዎች እንደሚሠራም አንስተዋል፡፡
ሌላው ሐሳባቸውን የሰጡት አቶ ኖህ ታከለ ናቸው። አቶ ኖህ በፍትሕ ሚኒስቴር የፍትሕ ስርዓት ማሻሻያና የለውጥ ሥር አመራር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ናቸው።

የግጭት አፈታት ላይ የባህላዊ ፍርድ ቤት ከፍተኛ ሚና እንዳለው ገልጸዋል። ማኅበረሰቡ በባህላዊ መንገድ ግጭቶች ለመፍታት ቅድሚያ እንደሚሰጥም አንስተዋል።
ባሕላዊ ፍርድ ቤቶች በቤተሰብ አባላትና በማኅበረሰብ መካከል የሚፈጠሩ ማኅበራዊ ግጭቶችን በመፍታት ይረዳሉ። እርቅና ሰላምን በቅርበት ለማውረድና አንድነትን ለማጠናከር የማይተካ ሚና እንዳለውም ይነሳል።
ሕብረተሰቡም በእምነት፣ በሃብትና በጎሳ ምክንያት ፍትሕ ይዛባብኛል ከሚል ስጋት ነጻ ሆኖ የሚዳኝበት ሥርዓት በመሆኑ ለፍትሕ መረጋገጥ አስተዋጽኦ እንዳለው ይነገራል።
አቶ ኖህ ታከለ ይህንን አሠራር በተለይም ግጭቶችን ለመፍታት በሁሉም ክልሎች የማዳረስ ሥራ እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ከመደበኛ ፍርድ ቤት ጎን ለጎን የመሠረተ ማኅበረሰብ ፍትሕን በማጠናከር ለሕብረተሰቡ የፍትሕ ጥያቄዎች ምላሽ እየተሰጠ መሆኑም በዛሬው ዕለት መድረክ ከተነሱ መካከል ነው። በዚህም ሕዝቡ በመሠረተ ማኅበረሰብ ፍትሕ አገልግሎት እንዲያገኝ ተደርጓል።
ለባህላዊ የግጭት አፈታትና ዳኝነት እውቅና እንዲሰጥ መደረጉም ተገልጿል። በዚህም ሕዝቡ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ለመፍታት ሲጠቀምባቸው የቆዩ የመሠረተ ማኅበረሰብ ፍትሕን የበለጠ በማጠናከር ሕዝቡ በቅርበት ፍትሕ እንዲያገኝ እየተደረገ መሆኑ ተነስቷል።
በኦሮሚያ ክልል ከሁሉም ክልል ቀድሞ ከአምስት ዓመት በፊት ይህንን ባህላዊ ፍርድ ቤት የጀመረ መሆኑ ተገልጿል። በዓመት እስከ 500 ሺሕ የሚሆኑ ጉዳዮች እንደሚመለከት ተብሏል።
ባህላዊ ፍርድ ቤት ለሕዝቡ ከፍተኛ የሆነ ጠቀሜታ በመኖሩ ሕዝቡ በሙሉ ልብ ተቀብሎታል ያሉት ደግሞ በኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ አቃቢ ሕግ ዋና ዳይሬክተር ኢብሳ ጨመዳ ናቸው።

በኦሮሚያ ክልል አዋጅ ከወጣ በኋላ ደንብ እና መመሪያ ማውጣት መቻሉን ገልጸዋል። ነገር ግን ለዳኞች ነፃነት አለመስጠት እና አዋጁን ተከትሎ ያለመስራት ተግዳሮቶች መኖራቸውን ያነሳሉ።
የሲዳማ "አፊኒ" ባህላዊ የዳኝነት ሥርዓት ከጥንት ጀምሮ በሲዳማ ማኅበረሰብ ዘንድ ተግባራዊ ሲደረግ የቆየ የባህላዊ እርቅና ፍትሕ ስርዓት ነው። ባህላዊው የ"አፊኒ ሶንጎ" አሁን ባህላዊ የዳኝነት ሥርዓት ተግባራዊ በማድረግ ሥራ ጀምሯል። በርካታ ጉዳዮችን እየተመለከተ መሆኑም ይነሳል።
በአሁኑ ወቅት በመደበኛነት አገልግሎት ላይ እንዲውል የክልሉ ምክር ቤት ባፀደቀው አዋጅ መሠረት ''አፊኒ'' ሥራ ጀምሯል።

የክልል ፍትሕ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አሽሌ ዳንኤል በበኩላቸው፤ ባህላዊ ፍርድ ቤት የሚመለከታቸው ጉዳዮች የተወሰነለት መሆኑን ያነሳሉ። በተለይም ከባድ የሆኑ የግድያ የመሰሉ ወንጀሎችን ይፈታሉ ማለት አይደለም። ይህ ማለት ግን የማስታረቅ ሥራውን አያከናውኑም ማለት አይደለም ይላሉ።
በሀገሪቱ የመሠረተ የማኅበረሰብ ፍትሕን በሁሉም አካባቢዎች ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑም ተገልጿል። ማህበረሰቡን መሠረት ያደረገ ባህላዊ ዳኝነት ግጭቶችን ከመፍታት በተጨማሪ እርቅ በመፍጠር ይረዳል። ይህም ማኅበረሰቡ መካከል ማኅበራዊ መስተጋብር የበለጠ እንዲጠናከር ያደርጋል ተብሏል።

ቤተልሔም ዳንኤል የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የፍትሕ ቢሮ ኃላፊ ናቸው። ይህ የባህላዊ ፍርድ ቤት ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው ያስረዳሉ። በተለይም ብዙ ርቀት ሳይጓዝ የማኅበረሰብ ክፍሉ በአቅራቢያው መፍትሔ የሚያገኝበትን መንገድ መፍጠሩን ኃላፊዋ አንስተዋል።
በዘመናዊ ፍርድ ቤቶች ለመዳኘት የሚወጣውን ወጪ ስለሚቀንስም ጥቅሙ ከፍተኛ መሆኑ በዛሬው ዕለት ከተነሱ ጉዳዮች መካከል ነው። በተጨማሪም ግጭቶችን ለመፍታት ዓይነተኛ ሚና የሚጫወት መሆኑም በውይይት መድረኩ ላይ ተገልጿል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ