ጥቅምት 3/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) ‌‎የተገልጋይ እንግልት ለመቀነስ፣ የመዝገብ መጥፋት እና ብልሹ አሰራሮችን ለማስቀረት ታስቦ የተዘጋጀው የዲጂታል አሰራር ከመስከረም 23 ቀን 2018 ጀምሮ በሰበር ችሎት በከፊል መጀመሩን የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ለአሐዱ አስታውቋል።

የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት ዳኛ አበበ ሰለሞን፤ አዲሱ የቴክኖሎጂ አሰራር ሙሉ ለሙሉ ወደ ትግበራ ሲገባ ባለጉዳዮች ባሉበት የችሎት አገልግሎት የሚያገኙበት በመሆኑ የተገልጋይን እንግልት ይቀንሳል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

አዲሱ የቴክኖሎጂ አሰራር በፍርድ ቤቶች ላይ ሙሉ ለሙ ተግባራዊ ለማድረግ ለዐቃቤ ሕግ ቢሮ፣ ለጠበቆች፣ ለአዲስ አበባ ፖሊስ፣ ለማረሚያ ቤቶች፣ ለተቋማት ባለሙያዎች እና አጠቃላይ ባለድርሻ አካላት የግንዛቤ ማስጨበጫ መሰጠቱንም አስታውቀዋል፡፡

ግንዛቤው ለሌላቸው ዜጎች ፍርድ ቤቶች ባለሙያ እንደሚመደብ ተገልጿል፡፡

በተያያዘ ከነሐሴ 1 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ በከፊል ዝግ ሆነው የቆዩት የፌደራል ፍርድ ቤቶች ከዛሬ ሰኞ ጥቅምት 3 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ መደበኛ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምሩ ምክትል ፕሬዝዳንቱ ገልጸዋል።

እንዲሁም በአዲስ አበባ አራት ኪሎ ባለው የኢትዮ-ፓስታ ሕንጻ ላይ አገልግሎት እየሰጠ የቆየው የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የፍትሐብሄር ይግባኝ ችሎት፤ ከዛሬ ጥቅምት 3 ቀን 2018 ጀምሮ አራት ኪሎ ከአብረሆት ላይብረሪ ወደ ፒያሳ መሄጃ 100 ሜትር ወረድ ብሎ ፍርድ ቤቱ እያስገነባ ወደሚገኘው አዲሱ ሕንጿ ተዛውሮ አገልግሎት መስጠት መጀመሩ ተገልጿል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ