ሕዳር 25/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የመረጃ ደህንነት ምክትል ዳይሬክተር ስዩም ዳምጠው እንደገለጹት የተለያዩ ጥናት እንደሚያሳዩት በኢሜል እና በተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያ አማራጮች ከሚላኩ መስፈንጠሪያዎች 50 በመቶው የሚሆነው ሰው ማጣራት ሳያደርግ ይጠቀማቸዋል።
በዚህም በቀላሉ መረጃዎች የሚወሰዱ መሆናቸውን ገልጸው፤ የተሰረቁ መረጃዎችን በማህበራዊ ትስስር ገጾች የሚያጋሩ ሰዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ 4 ነጥብ 8 ሚሊየን መድረሳቸውን አንስተዋል።

ስለሆነም በቅድሚያ ሁሉንም ነገሮች ማረጋገጥና የማይታወቁ ምንጮችን አለመጠቀም "ዜሮ ትረስት" አስፈላጊ ነው ብለዋል።
በቀደመው ጊዜ መሰል ጥቃቶችን ለመከላከል ከውጭ ወይንም ከኢንተርኔት የሚመጡ ነገሮችን አለማመን ሲሆን፤ 'ከቅርብ ሰዎች ግን ከሆነ ችግር የለውም' የሚል እሳቤን በመቀየር አሁን ሁሉንም አለማመን ዜሮ ትረስት መርህን መከተል አስፈላጊ ነው ይላሉ።
በዚህም በቀላሉ የሚመጡ የተለያዩ ጥቃቶችን መከላከል እንደሚቻል አንስተው፤ በየዓመቱ 40 በመቶ የሚሆን የሚስጥራዊ መረጃዎች ስርቆት ይፈጸማል ብለዋል።
በተለይም መረጃ የሚቀመጥበት "ፐብሊክ ክላውድ" ላይ መሰል ጥቃቶች መኖራቸውን እነዚህን አገልግሎት በመጠቀም ሂደት ውስጥ አገልግሎት አቅራቢው የሚሰጣቸውን ኃላፊነቶች በመወጣት ከመረጃ ስርቆት መጠበቅ እንሚገባ ገልጸዋል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ