መስከረም 12/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) ሰው ሰራሽ አስተውሎትን (ኤአይን) ለበጎ አላማ መጠቀም እንደሚገባ የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት አሳስቧል።

ኢንስቲትዩቱ ለማህበረሰቡን ግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራን በመስራት ላይ እንደሚገኝ ለአሐዱ አስታውቋል።

የኢንስቲትዩቱ የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር ተስፋዬ ዘውዴ፤ በሰው ሰራሽ አስተውሎት ወይንም (ኤአይ) ቴክኖሎጂ ዘርፍ በአህጉር አቀፍ ገና ጅማሬ ላይ ነን ሲሉ ገልጸዋል።

Post image

በአንፃሩ ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ሀገራት ቀድማ መጠቀም የጀመረችና ብሔራዊ ፓሊሲ በመቅረፅ ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል፡፡

በዚህም ተቋሙ ከተመሠረተ ጊዜ ጀምሮ በሰው ሰራሽ አስተውሎት ችግሮችን ለመፍታት እየሰራ መሆኑን ያነሱ ሲሆን፤ የሀገርን ችግሮች የሚፈቱ እና የዜጎችን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።

ለአብነትም የአንድ መሶብ አገልግሎት ላይ ኢንስቲትዩቱ በሶፍትዌር ማበልጸጉ ላይ መሳተፉንና ይህም የአገልግሎት ዘርፉን ወደ አንድ ደረጃ ከፍ ያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

"ሆኖም አሁንም መሻገር ያሉብን ችግሮች አሉ" ያሉ ሲሆን፤ የተማረና በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ሀይል መፍጠር ላይ በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።

የመረጃ አቅርቦት መሻሻሎች ቢኖሩትም አሁንም በቂ አለመሆኑን ገልጸው፤ በዚህ ላይ ተቋማት ሊተባበሩ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

በተጨማሪም የሰው ሰራሽ አስተውሎትን ሥራ የተረዳ ማህበረሰብ እንዲኖር ለማድረግ የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራዎች መኖራቸውናን ከመገናኛ ብዙኃን ጋርም በጋራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ይህ ሲሆን ግን ሥነ-ምግባርን በጠበቀ እና ለበጎ አላማ የሰውን ሕይወት ሊያሻሽል፣ ሊያሳድግ እና ሊቀይር በሚችል መልኩ መጠቀም እንደሚያስፈልግ ዳይሬክተሩ አፅንዖት ሰጥተውበታል።

በተጨማሪም 'የሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ አያስፈልግም' ማለት ስለማይቻል ለመልካም እና መሻሻልን በሚያመጣ መልኩ መጠቀም ይገባል ብለዋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ