ጥቅምት 11/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ለጤና ተቋማት በብድር መልክ፤ ከ8 ቢሊየን ብር በላይ የዋጋ ግምት ያላቸውን መድኃኒቶች እና የሕክምና መገልገያ መሳሪያዎች ማሰራጨት ቢችልም፤ ከዚህ ውስጥ 1 ቢሊየን ብር በላይ አለመሰብሰቡን ለአሐዱ አስታውቋል።

በዋናነት የተቋሙ ዓላማ ትርፍን መሰረት አድርጎ አገልግሎት መስጠት ባለመሆኑ ሕብረተሰቡ ተጠቃሚ እንዲሆን በማቀድ ብዙ ብድር ለተቋማት እንደሚሰጥ፤ የአገልግሎቱ ምክትል ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ንጉሤ ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡

አሁን ላይ በተለያዩ ምክንያቶች ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ የመድኃኒት እና የሕክምና መሳሪያዎች የሽያጭ ገንዘብ ከተቋማት አለመሰብሰቡን በመግለጽም፤ የተሰራጨው የግብዓት ገንዘብ በጊዜ አለመሰብሰቡ በተቋሙ ግዢ ስርዓት ላይ ተፅዕኖ ያሳድራል ብለዋል።

ከዚህን ቀደም በነበረው የብድር ውል ከተቋማት የሽያጭ ገንዘብ ለመሰብሰብ አስገዳጅ አለመሆኑን የጠቆሙት ምክትል ዳይሬክተሩ፤ ዘንድሮ ተግባራዊ የተደረገው ልዩ የግዥ መመሪያ ብድር መመለስን አስገዳጅ ስለሚያደርግ መሰብሰብ ያለበትን ክፍያ ተቋሙ እንደሚሰበስብ ጠቁመዋል።

በመመሪያ ቁጥር 1066/2017 ዓ.ም መሰረት የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ወደ ሥራ ያስገባው መመሪያ፤ መሰል ችግሮችን ለመቅረፍ አስቻይ ማድረጉን ገልጸዋል።

በተጨማሪም የመድኃኒት አቅርቦት ሰንሰለቱን መሰረታዊ ችግሮች መቅረፉን እና ለሀገር ውስጥ አምራቾች ከፍተኛ ትኩረት እንዲሰጥ ማድረጉን ነግረውናል።

የተለየ የመድኃኒት የግዥ መመሪያ ያስፈለገበትን ምክንያት ምክትል ዳይሬክተሩ ሲያብራሩ፤ ለተለዋዋጭ የጤና ፍላጎት፣ ለሰው ሠራሽና ተፈጥሯዊ ድንገተኛ የጤና አደጋዎች እንዲሁም፤ በጤናው ዘርፍ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ለመጣው የማህበረሰብ የጤና መድህን ተጠቃሚ ፍላጎት ወቅታዊና ፈጣን ምላሽ ከመስጠት እና የመድኃኒት ተደራሽነትን ከማስፋት አንፃር መንግሥት የሀገር ውስጥ የመድኃኒት አምራቾችን ለማበረታታት ታቅዶ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም መድኃኒት እና የሕክምና መሳሪያዎች ከግዥ አፈፃፀማቸው ጀምሮ እስከ አጠቃቀማቸው ልዩ ጥንቃቄ የሚጠይቁ በመሆኑ፤ ይህንን ልዩ ባህሪ ታሳቢ ያደረገና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተደገፈ ስትራቴጂያዊ የግዥ አሰራር መዘርጋት አስፈላጊ እንደነበረ አስታውሰዋል።

የግዥ መመሪያው በዓለም አቀፍ ግልፅ ጨረታ ግዥ መፈፀም የሚቻልበት የገንዘብ ጣሪያ 3 ቢሊዮን ብር መደረጉን፣ የውስን ጨረታ የገንዘብ ጣሪያ 2 ቢሊየን ብር እንደሆነ እንዲሁም፤ የጨረታ ቆይታ ጊዜ ለብሔራዊ ግልፅ ጨረታ 15 ተከታታይ ቀናት፣ ለዓለም አቀፍ ግልፅ ጨረታ 21 ተከታታይ ቀናት እና ለውስን ጨረታ ደግሞ 10 ተከታታይ ቀናት እንደሆነ በመመሪያው መቀመጡን አስታውሰዋል፡፡

ይህም የጨረታ ግዥ መመሪያ ከአሁን በፊት ለግዥ ይወስድ የነበረውን ጊዜ ያሳጠረው መሆኑን አስረድተዋል፡፡

መመሪያው የሀገር ውስጥ አምራቾችን በእጅጉ የሚያበረታታ እና ተጠቃሚ የሚያደርግ ሲሆን፤ የረጅም ጊዜ የአቅርቦት ውል በማስገባት ጥሬ እቃ በሀገር ውስጥ በመጠቀም እንዲመርቱ ዕድል እንደሚፈጥር ታምኖበታል፡፡

ሆኖም ግን ሁሉንም አማራጮች በመጠቀም በሀገር ውስጥ አምራቾች ግብአቶች መቅረብ ካልተቻሉ፤ ከውጭ ገበያ ለሟሟላት አማራጭችን አስቀምጧል።

በተያያዘ በ2017 በጀት ዓመት 64 ቢሊዮን ብር የሚያወጡ ክትባቶች፣ የጤና ኘሮግራም ግብዓቶች፣ መሰረታዊ መድኃኒትና የሕክምና ግብዓቶች መሰራጨራተቸውን የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት አስታውቋል።

አግልግሎቱ ከ22 ሺሕ በላይ ለሆኑ ለመንግሥት ጤና ተቋማት የሕክምና መገልገያ መሳሪያዎች ፣መድኃኒቶችን ተቋሙ ተደራሽ እያደረገ መሆኑን ገልጿል።

የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት የደንበኛ እና ባለድርሻ አካላት ፍላጎትን ለማሳደግ፣ የአቅርቦት ሰንሰለት ዕቅድና ትንተና በማጎልበት፣ የተሳለጠ የግዢ ስዓት ማሻሻያ በመተግበር፣ የመጋዘን አስተዳደር በማዘመን፣ የጤና ተቋማት የመድኃኒት ትዕዛዝና ስርጭት ሂደትን ለማጎልበት በርካታ ስራዎች በመስራት ውጤታማ እንደሆነ ተጠቁሟል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ