ጥቅምት 11/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር በቴክኒክና ሙያ ዘርፍ እንደሀገር ለመጀመሪያ ጊዜ በደረጃ 8 ወይንም በዶክትሬት(ፒ.ኤች.ዲ) ደረጃ ስልጠና መሰጠት መጀመሩን አስታውቋል።
በደረጃ 8 ወይንም በዶክትሬት(ፒ.ኤች.ዲ) ደረጃ የሚሰጠው ይህ ስልጠና፤ ዘርፉን ለወጣቶች ምቹና ሳቢ እንዲሆን ከማድረግ ባሻገር ለሙያ ስልጠና ፍላጎቱና ተሰጥኦው ላላቸው ዜጎች በመረጡት የሙያ መስክ ከጀማሪ ሙያተኛ እስከ ከፍተኛ ሙያተኛ የመሆን ዕድሉን የሚፈጥር መሆኑም ተገልጿል።
ሚኒስቴሩ በ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ውጤታቸው መሠረት በ2018 ዓ.ም ወደ ቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ተቋማት የሚገቡ ሰልጣኞች የመግቢያ ነጥብ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር በትናትናው ዕለት በሰጠው መግለጫ ይፋ አድርጓል፡፡

በተዘጋጀው የመቁረጫ ነጥብ መሰረት በ2018 ዓ.ም የትምህርት ዘመን 454 ሺሕ 106 ተማሪዎች የቴክኒክና ሙያ ዘርፉን ይላቀላሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጿል።
በዚህም 2018 ዓ.ም የስልጠና ዘመን ወደ ቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ተቋማት የሚገቡ ሰልጣኞች የመግቢያ ነጥብ በ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ውጤታቸው መሰረት ለተፈጥሮና ማህበራዊ ሳይንስ የመግቢያ ውጤት ከደረጃ 1 እስከ 5 በዝርዝር አስቀምጧል።
በመግቢያ ውጤት ዝርዝሩም መሠረት የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ እና ቅድመ ዝግጅትን ወይንም የ12ኛ ክፍል ላጠናቀቁ ለደረጃ1 እና ደረጃ2 ሰልጣኞች መቁረጫ ነጥብ ሲያስቀምጥ፤ ለወንዶች አርብቶ አደር አካባቢዎችን ሳይጨምር 134 እና ከዚያ በታች፣ ለወንዶች አርብቶ አደር አካባቢዎች 132 እና ከዚያ በታች፣ ሴቶች አርብቶ አደር አካባቢዎችን ሳይጨምር 121 እና ከዚያ በታች፣ ሴቶች አርብቶ አደር አካባቢዎች 120 እና ከዚያ በታች እንዲሁም ለሁሉም ክልል አካል ጉዳተኞች 120 እና ከዚያ በታች ሆኖ መመረጡን ሚኒስቴሩ አመላክቷል።
እንዲሁም የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ እና ቅድመ ዝግጅት ወይንም 12ኛ ክፍል ላጠናቀቁ ደረጃ 3 እና ደረጃ 4 ሰልጣኞች ደግሞ ወንዶች አርብቶ አደር አካባቢዎችን ሳይጨምር 135 እና ከዚያ በላይ፣ ወንዶች አርብቶ አደር አካባቢዎች 133 እና ከዚያ በላይ፣ ሴቶች አርብቶ አደር አካባቢዎችን ሳይጨምር 122 እና ከዚያ በላይ፣ ሴቶች አርብቶ አደር አካባቢዎች 121 እና ከዚያ በላይ እንዲሁም፤ ለሁሉም ክልል አካል ጉዳተኞች 121 እና ከዚያ በላይ ሆኖ ተቀምጧል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ ለደረጃ 5 ሰልጣኞች መቁረጫ ነጥብ ደግሞ ወንዶች አርብቶ አደር አካባቢን ሳይጨምር 179 እና ከዚያ በላይ፣ ወንዶች አርብቶ አደር አካባቢዎች 168 እና ከዚያ በላይ፣ ሴቶች አርብቶ አደር አካባቢን ሳይጨምር 168 እና ከዚያ በላይ፤ ሴቶች አርብቶ አደር አካባቢ 157 እና ከዚያ በላይ፤ ለሁሉም ክልል አካል ጉዳተኞች 142 እና ከዚያ በላይ ሆኖ መመረጡን የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ይፋ አድርጓል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ