ሕዳር 12/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) አይደር ሪፈራል ሆስፒታል ያለበትን ከፍተኛ የመድኃኒት እጥረት ለማቃለል ከኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ጋር ውል ቢገባም፤ በሩብ ዓመቱ ከሚያስፈልገው ለሕክምና የሚውል መድኃኒት 75 በመቶው እንዳልተሟላለት አስታውቋል።
ሆስፒታሉ የመድኃኒት አቅርቦት እጥረቱን ሙሉ ለሙሉ ለመፍታት በተፈራረመው ስምምነት መሠረት መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎቱ ከአስፈላጊ መድኃኒቶች መካከል 80 በመቶውን በቁጥር፤ ቀሪውን 20 በመቶ ደግሞ በአይነት የማቅረብ ግዴታ ይጥላል። ይሁንና ከሚጠበቀው አቅርቦት በ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያው ሩብ ዓመት ለሆስፒታሉ የቀረበው 25 በመቶው ብቻ ነው ተብሏል።
የአይደር ሪፈራል ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር አብርሃ ገብረእግዚአብሔር ፤ "መድኃኒት አቅራቢው የፍላጎቱን 50 በመቶ ማቅረቡን ቢገልጽም፤ ለሆስፒታሉ በትክክል የቀረበለት ግን 25 በመቶ ብቻ ነው" ብለዋል።
ይህም መድኃኒቶች በተፈለገው ጊዜና መጠን ያለመገኘታቸው ችግር በሆስፒታሉ መድኃኒት ከታዘዘላቸው ታካሚዎች መካከል 43 በመቶ የሚሆኑት፤ በተጋነነ ዋጋ ከውጭ እንዲገዙ እያስገደደ መሆኑን አብራርተዋል።
በቀጣይነት አሁን ያጋጠመው ችግር በሁለተኛው ሩብ ዓመት እንዳይደገም፤ ከአገልግሎት ተቋሙ ጋር በመነጋገር ለመፍታት ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ሜዲካል ዳይሬክተሩ ለአሐዱ ሬዲዮ ተናግረዋል።
የሁለቱ ተቋማት የተለየ ስምምነት መፈራረም ያስፈለጋቸው፤ እጅ በእጅ ክፍያ ሳይፈጽሙ በዱቤ የሚወሰዱ ተቋማት ቁጥር እየበዛ በመምጣቱ እና እዳዎች በወቅቱ ባለመሰብሰባቸው የግዥ ሥርዓቱ ላይ መስተጓጎል እየፈጠረ በመምጣቱ ምክንያት እንደሆነ የኢትዮጵያ መድኃኒት አገልግሎት ማስታወቁ ይታወሳል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
አይደር ሪፈራል ሆስፒታል በሩብ ዓመቱ ከሚያስፈልገው መድኃኒት 75 በመቶው እንዳልቀረበለት ገለጸ