ሕዳር 12/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) በዱባይ የአየር ትርዒት (Dubai Airshow) በማሳያ በረራ ላይ የነበረው የህንድ ተዋጊ ጀት አውሮፕላን ተከስክሶ የአውሮፕላኑ አብራሪ ሕይወቱ ማለፉን የህንድ አየር ኃይል አስታውቋል፡፡
የህንድ አየር ኃይል ንብረት የሆነው ቴጃስ ተዋጊ አውሮፕላን ዛሬ በዱባይ አል ማክቱም ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የአየር ትርዒት እየሳየ በነበረበት ወቅት የተከሰከሰ ሲሆን፤ በአደጋው የህንድ አየር ኃይል አብራሪ ሕይወቱ አልፏል፡፡

የህንድ አየር ኃይል በሀገር ውስጥ የተመረተው 'ቴጃስ' ቀላል ተዋጊ ጀት ሲሆን፤ በአየር ትርዒቱ ላይ የክህሎት በረራ በሚያደርግበት ወቅት በድንገት ከፍታ አጥቶ መሬት ላይ መከስከሱ ነው የተገለጸው።
አደጋው በሚሊዮን በሚቆጠሩ የትርዒቱ ታዳሚዎች ፊት የተከሰተ ሲሆን፤ አውሮፕላኑ ሲከሰከስ ከፍተኛ የእሳት ኳስ ታይቶ ወፍራም ጥቁር ጭስ ወደ ሰማይ መውጣቱ በዓይን እማኞች ተገልጿል።

የዱባይ ሚዲያ ቢሮ የእሳት አደጋ እና የአደጋ ጊዜ ቡድኖች በፍጥነት ወደ ስፍራው ደርሰው ሁኔታውን መቆጣጠራቸውን ያስታወቀ ሲሆን፤ ትርዒቱ ለጊዜው ተቋርጦ ጎብኝዎች ወደ ኤግዚቢሽን አዳራሾች እንዲመለሱ ተደርጓል።
አደጋውን ተከትሎም የህንድ አየር ኃይል በደረሰው የሕይወት መጥፋት ጥልቅ ሀዘን እንደተሰማው ገልጾ፤ የአደጋው መንስኤ ለማጣራት የምርመራ ኮሚቴ በማቋም ምርመራ መጀመሩን በኤክስ ገጹ አስታውቋል።

ይህ አይነት ክስተት በዱባይ የአየር ትርዒት ታሪክ ውስጥ እምብዛም የማይታይ ቢሆንም፤ የህንድ አየር ኃይል በአጠቃላይ በተለያዩ ጊዜያት በአውሮፕላን አደጋዎች አብራሪዎቹን አጥቷል።
ከእነዚህም ውስጥ እ.ኤ.አ በሐምሌ ወር 2025 በምዕራብ ህንድ ራጃስታን ግዛት የጃጓር ማሰልጠኛ ተዋጊ ጀት ወድቆ ሁለቱም አብራሪዎች ሕይወታቸው ያለፈ ሲሆን፤ በተመሳሳይ በሚያዚያ 2025 በጉጃራት ግዛት ውስጥ የጃጓር ተዋጊ ጀት ተከስክሶ አንድ አብራሪ ሕይወቱ ማለፉ ይታወሳል፡፡
'ቴጃስ' ህንድ እራሷ የነደፈችውና ያመረተችው ዘመናዊ ተዋጊ ጀት ሲሆን፤ የሀገሪቱ የመከላከያ አቅም ማሳያ እና የ"Make in India" (በህንድ ውስጥ መሥራት) ስትራቴጂ ዋና አካል ነው።
አውሮፕላኑ በዚህ የዓለማችን ትልቁ የአየር ትርዒት ላይ መሳተፉ ህንድ ጄቱን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማስተዋወቅ በምታደርገው ጥረት ወሳኝ እንደነበር ተገልጿል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ