ሕዳር 2/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) አማኑኤል የአዕምሮ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በ2018 በጀት ዓመት በ1ኛ ሩብ ዓመት ለ32 ሺሕ 084 ተገልጋዮች በአዕምሮ ሕመምና እና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ የሕክምና አገልግሎቶች መስጠቱን አስታውቋል፡፡

በዚህም በአስተኝቶ የአዕምሮ ሕክምና 450፣ በተመላላሽ የአዕምሮ ሕክምና 30 ሺሕ 934 እንዲሁም በድንገተኛ የአዕምሮ ሕክምና 700 ለሚሆኑ ሕሙማን አገልግሎት መስጠቱን ገልጿል።

በተጨማሪም በ2018 በጀት 1ኛ ሩብ ዓመት ውስጥ 125 የሚሆኑት ሕጻናት የአዕምሮ ሕክምና ያገኙ ሲሆን፤ በሱስ ሕክምና ደግሞ 50 ለሚደርሱ ዜጎች የሕክምና አገልግሎቱን መስጠት መቻሉን ሆስፒታሉ ለአሐዱ ሬዲዮ በላከው መግለጫ አስታውቋል፡፡

ከዚህ ጎን ለጎን ሆስፒታሉ ከሚሰጣቸው አገልግሎቶች ውስጥ የፋርማሲ አገልግሎትን ማሻሻል በኩል የመድኃኒት ብክነት መቀነስ መቻሉን የገለጸው ሆስፒታሉ፤ መሠረታዊ መድኃኒት በበቂ ሁኔታ መኖሩ ታካሚዎች የታዘዘላቸውን መድኃኒቶች ማግኘት እንደቻሉ አስታውቋል።

በተጨማሪም ሆስፒታሉ የፎረንሲክ ሕክምና የወንጀልና የፍትሐብሔር ተመርማሪዎች በተመላላሽና በተኝቶ ማከም 142 ለሚሆኑ አገልግሎቱ ሲሰጥ፤ የማህበራዊ አገልግሎት ያገኙት ደግሞ በቁጥር 109 ናቸው ብሏል።

ከማህበራዊ አገልግሎት መካከል ቤተሰብ የሌላቸውን ታካሚዎች ለእርዳታ ድርጅቶች መስጠት፣ ከሕክምና በኋላ ከሆስፒታሉ ወደ ቤተሰባቸው መቀላቀል እንዲሁም፤ የሕይወት ክህሎት ትምህርት መስጠትና ሆስፒታል ግቢ ውስጥ ሲመጡ ድጋፍ ማድረግ እንደሚገኙበት ገልጿል።

በዚህም በሆስፒታል ጤና ጣቢያ ጥምረት ለጥራት፤ በሥነ አዕምሮ ሕክምናና የጥራት ማሻሻያ ፕሮጀክት ፅንሰ ሃሳብና ትግበራ በተመለከተ፤ በአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር ሥር በሚገኙ 17 ጤና ጣቢያዎች ላይ የስልጠናና ተከታታይ ድጋፍ እየሰጠ መሆኑን ገልጿል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ