ሕዳር 2/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) ከ40 ሺሕ ሕዝብ በላይ ይሳተፍበታል ተብሎ የሚጠበቀው 5ኛው ሀገር አቀፍ የሠላም ጉባኤ "ሐይማኖቶች ለሠላም፤ ለአንድነትና ለአብሮነት" በሚል መሪ ቃል በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በአርባምንጭ ከተማ ነገ ሕዳር 3 እና 4 ቀን 2018 ዓ.ም እንደሚካሄድ የኢትዮጵያ ሐይማኖት ተቋማት ጉባኤ አስታውቋል።
የኢትዮጵያ ሐይማኖት ተቋማት ጉባኤ ዋና ፀሐፊ ሊቀ ትጉኃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ፤ ከዚህ ቀደም በድሬዳዋ፣ በጅማ፣ በባህርዳር እና በሀረሪ ከተማ ሀገር አቀፍ የሰላም ጉባኤው መካሄዱን አስታውሰው፤ 5ኛው ሀገር የሰላም ጉባኤ ደግሞ በአርባምንጭ ከተማ ለሁለት ቀናት እንደሚካሄድ ተናግረዋል።
የሠላም ጉባኤው ዓላማ በሀገሪቱ አንድ አንድ አካባቢዎች የሚስተዋለውን ግጭት እና አለመግባባት ለማስቆም የሚደረግ ጥረትን ማገዝ፣ ግጭቶችን በጥበብ የመፍታት ልምድን ለማሳደግ፣ የሐይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች በተግባር እና በታማኝነት እንዲሰሩና እንዲወጡ ለማድረግ እንዲሁም፤ ሕዝቡ ስለሠላም በአንድነት እንዲቆም ማድረግ መሆኑን ዋና ፀሐፊው ገልጸዋል።
በአርባምንጭ ከተማ የሚካሂደው የሰላም ጉባኤ ላይ ከ30 ሺሕ እስከ 40 ሺሕ ሕዝብ ይሳተፋል ተብሎ ይጠበቃል ያሉት ዋና ፀሐፊው፤ በጉባኤውም ሁለት ዋና ዋና ኩነቶች የሚደረጉ ሲሆን ሕዝባዊ የውይይት መድረክ እና ሰላምን ለማፅናትና ለማረጋገጥ ጥልቅ ምክክር ይደረጋል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ሐይማኖት ተቋማት ጉባኤ ከዚህ ቀደም በተደረጉ የሰላም ጉባኤዎች የአባቶችንና የሀገር ሽማግሌዎችን ምክርና ሀሳብ ተቀብለው የትጥቅ ትግል ሲያደርጉ የነበሩ ታጣቂዎችና በአንድ አንድ አካባቢ ያሉ ኃይሎች የሠላም ጥሪ ተቀብለው ወደ ሰላም ተመልሰዋል ሲሉ ሊቀ ትጉኃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ ተናግረዋል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
ከ40 ሺሕ በላይ ሕዝብ የሚሳተፍበት 5ኛው ሀገር አቀፋ የሠላም ጉባኤ በአርባ ምንጭ ከተማ እንደሚካሄድ ተገለጸ