ሕዳር 1/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) 10ኛው ሀገር አቀፍ የተማሪዎችና የመምህራን የፈጠራ ሥራ ውድድር እና አውደ ርዕይ "የዓለም ሳይንስ ቀን ለሰላምና ልማት" በሚል መሪ ቃል በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ቅጥር ግቢ በዛሬው ዕለት በይፋ ተጀምሯል።
ትምህርት ሚኒስቴር ለተከታታይ 9 ዓመታት የመምህራንና የተማሪዎች የፈጠራ ሥራ ውድድር እና አውደ ርዕይ ሲያካሂድ መቆየቱ ይታወቃል።
የሚኒስቴሩ ሚኒስቴር ዴታ አየለች እሸቴ ለአሐዱ ሬዲዮ እንደተናገሩት፤ ይህ የውድድር እና አውደ ርዕይ ለተከታታይ 5 ቀናት ይቆያል።

ሚኒስቴሩ ለፈጠራ እና ምርምር ሥራ ትኩረት በመስጠት አዲስ የትምህርት ስርዓት በመቅረፅ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
የዓለም የሳይንስ ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ26ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ10ኛ ጊዜ እየተከበረ መሆኑን አንስተው፤ በኢትዮጵያ የቴክኖሎጂ እና የፈጠራ ቀን ሲከበር የሕብረተሰብን ችግር መፍትሔ መስጠት እንዳለበት ተናግረዋል።
በውድድሩ ተሳታፊ የሆኑ ተወዳዳሪዎች ከ11 ክልሎች እና ከ36 ዩንቨርስቲ የተውጣጡ መምህራን እና ተማሪዎች ሲሆኑ፤ በውድድሩም 138 ፕሮጀክቶች ቀርበዋል።
ውድድሩ የመምህራን እና ተማሪዎችን ተሰጦን እና ፍላጎት መሠረት ያደረገ መሆኑን የገለጹት ሚንስትር ዴኤታዋ፤ ይህ መሆኑ ተማሪዎች ትስስር መፍጠር እንዲችሉ እንደሚያደርጋቸው ገልጸዋል።

የፈጠራ ሥራ የሚያቀርቡ ተማሪዎች ለ2 ወር እና 3 ወር ስልጠና በመስጠት ወጣቶች የአካባቢያቸውን ችግር እንዲያጠኑ በማድረግ የፈጠራ ሥራ እንዲያቀርቡ መደረጉን አንስተው፤ ይህ በመሆኑ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ መሆን የሚችሉ ወጣቶችን ማፍራት መቻሉን ተናግረዋል።
አክለውም የተሰሩት የፈጠራ ሥራዎች የአካባቢን ችግር መፍታት የሚችል መሆን እንዳለበት አሳስበዋል።
በዚህም መሠረት እስከ ሕዳር 5 ቀን 2018 ዓ.ም. ድረስ የውድድሩን አሸናፊዎች ለመለየት የፈጠራ ሥራዎቹ ምዘና እንደሚደረግባቸው ተነግሯል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ