መስከረም 28/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) በዓለም አቀፍ ደረጃ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ለመከላከል በየዓመቱ እንደሚተገበር እና ይህንን በማስመልከት ሀገር አቀፍ የንቅናቄ መርሃ-ግብር መጀመሩን ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።
የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ደረጀ ድጉማ (ዶ/ር) በዛሬው ዕለት ለጋዜጠኞች በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንደገለጹት በተለይ የጡት ካንሰር የዓለም ዓይን ቀን እና የዓለም አዕምሮ ቀን በማስመልከት የነጻ ምርመራ፣ ሕክምና እና ለከፋ ችግር ሳይጋለጡ የግንዛቤ ማስጨበጫ ለመስጠት እንደሆነ አብራርተዋል።
የጡት ካንስር በሽታ በኢትዮጵያ ቀላል የማይባል ሰዎችን እንደሚያጠቃ የገለጹም ሲሆን፤ ለዚህም አብዛኛው ታማሚ በሽታው ከፍ ካለ በኋላ ወደ ሕክምና ስለሚመጡ ለችግር ተጋላጭ እንደሆኑ ተናግረዋል።

እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ ከ1 ቢሊዮን በላይ ሰዎች ለእይታ ችግር እንደተጋለጡም ሚኒስትር ዴታው ተናግረዋል።
በተለይ ባላደጉ ሀገራት ላይ በቀላሉ በመታከም ሊድኑ የሚችሉ ሰዎች ወደ ጤና ሕክምና ባለመሄዳቸው እና ቶሎ ባለመታየታቸው የችግሩ መንስኤም እንደሆነ የዓለም ጤና ድርጅት ያወጣውን መረጃ ዋቢ በማድረግ ገልጸዋል።
የዓለም የአእምሮ ጤና ቀን ከ33 ዓመት በፊት ለመጀመሪያ ጊዜ እ.ኤ.አ 1992 መስከረም 30 ወይም ኦክቶበር 10 ታስቦ የዋለ ሲሆን፤ ከዚያ ጊዜ ወዲህ በየዓመቱ በዚሁ ቀን ታስቦ ይውላል ብለዋል።
የዘንድሮ ክብረ በዓል የዓለም የአእምሮ ጤና ፌደሬሽን መሪ ቃል በመያዝ፤ "የአእምሮ ጤና አገልግሎትን በድንገተኛ እና ከፍተኛ አደጋ ወቅት ተደራሽ እናድርግ" (Access to service: Mental Health in Catastrophes and Emergencies) በሚል መሪ ቃል እንደሚከበር ገልጸዋል።
አክለውም የአእምሮ ጤና ችግር ያለባቸው ሰዎች ቁጥር በርካታ እንደሆነም ተናግረዋል።
ይህንን በማስመልከት በዛሬው ዕለት በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ጤና ጣቢያ የዓይን እና የጡት ካስር ምርመራውን በይፋ መጀመሩ ተመላክቷል።
ከዛሬ ጀምሮም በመላው ሀገሪቱ በጥቅምት ወር የምርመራ እና ግንዛቤ ማስጨቀጫ ሥራዎች እንደሚከናወኑ ገልጸዋል።
ሁሉም ማኅበረሰብ ወደ ጤና ማእከል በመሄድ ምርመራ ማደረግ እንደሚገባውና ጤንነቱን ማረጋገጥ እንዳለበት ተናግረዋል።
እንዲሁም በየዓመቱ ከማክበር በዘለለ ችግሮችን በመለየት ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት ጥረት እየተደረገ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ግብአቶችን በማሟላት ሥራዎች ላይ ትኩረት ተደርጎ እንደሚሰራም አስታውቀዋል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ