መስከረም 28/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) አፍሪካ እንደአህጉር ከተረጂነትና ከጥገኝነት እንድትወጣ ለማድረግ የአባል ሀገራቱን የውስጥ አቅም ማሳደግና ግብርን በትክክል መሰብሰብ እንደሚያስፈልግ የአፍሪካ አቅም ግንባታ ፋውንዴሽን ዋና ፀሃፊ ማማዶ ቢተየ ገልጸዋል፡፡
ዋና ፀሀፊው ይህንን ያሉት "ከግብር ወደ ተግባር፤ በአፍሪካ የመንግሥት ፋይናንስ አስተዳድር ላይ የሚስተዋለውን የፖሊሲና የትግበራ ክፍተት መሙላት" በሚል መሪ ቃል በዛሬው ዕለት በሸራተን አዲስ ሆቴል በተካሄደው "የአፍሪካ ቲንክ ታንክ" ጉባኤ መክፈቻ መርሓ ግብር ላይ ነው፡፡
ከዛሬ ጀምሮ ለሦስት ቀናት በሚካሄደው የአፍሪካ ቲንክ ታንክ ጉባኤ ላይ ንግግር ያደረጉት ዋና ፀሃፊው፤ አፍሪካ ከተረጂነትና ጥገኝነት እንድትወጣ ያላትን ሀብት በአግባቡ በመጠቀም የውስጥ አቅሟን ማጎልበትና ግብርን በተገቢው መልኩ መሰብሰብ ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብለዋል፡፡

ግብር በትክክል ከተሰበሰበ መንግሥታት መሠረተ ልማት ለመዘርጋትና እድገትን ለማፋጠን የሚያስችላቸውን የውስጥ አቅም መፍጠር ይችላሉ ያሉት ቢተየ፤ ይህ ሳይሆን ሲቀር ግን በውጭ እርዳታና ብድር ላይ ጥገኝ ይሆናሉ ብለዋል፡፡
ከዚህ አንጻር ሲታይ በአፍሪካ ሀገራት ሊሰበሰብ የሚታቀደው የግብር መጠንና በተግባር ገቢ የሚደረገው ሲነፃፀር ከፍተኛ ልዩነት የሚታይበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በዚህም አህጉሪቱ ያላትን እምቅ አቅም በተገቢው መንገድ በመጠቀም የዜጎችን አቅም በማጠናከር የተሻለ ግብር መሰብሰብ ከተረጂነትና ጥገኝነት ጋር ተያይዞ የሚመጣውን የውጭ ሀገራት ጣልቃ ገብነት መከላከልና ሉዓላዊነትንም ማስከበር ይቻላል ሲሉ ጠቁመዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም አሁን በአህጉሪቱ እየተሰበሰበ ያለው ግብር ከሌሎች አህጉራት ጋር ሲነፃፀር እዚህ ግባ የሚባል አይደለም ብለዋል፡፡

ይህ ጉባኤ የአፍሪካ አቅም ግንባታ ፋውንዴሽን (ACBF) ከአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን (AUC) እና ከአፍሪካ አመራር የልህቀት አካዳሚ ጋር በመተባበር ያዘጋጁት ሲሆን፤ ከ50 ሀገራት የተወከሉ 300 የሃሳብ መሪዎች፣ ፖሊሲ አውጪዎች፣ የግሉ ዘርፍ አንቀሳቃሾችና የልማት አጋሮች እየተሳተፉበት ይገኛል፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ