ሰኔ 24/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ብሔራዊ የጤና ኢኖቬሽን ማበልጸጊያ ማዕከል በቅርቡ ሥራ እንደሚጀምር የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ሚኒስቴር ለአሐዱ ገልጿል።
የጤና ሚኒስቴር እና የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ሚኒስቴር በጋራ በመሆን፤ የጤና ስርዓቱን ለማዘመንና በጤናው ዘርፍ ያሉ ፈጠራዎችን የአገልግሎት ጥራት እና ተደራሽነትን ለማሳደግ የሚረዱ ሀሳቦችን ለማመንጨት የሚያስችሉ ሥራዎችን እየሰሩ መሆኑ ይታወቃል።
የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር በለጠ ሞላ እንደገለጹት፤ በኢኖቬሽን፣ በፈጠራ ባለሙያዎችና ሌሎች አጋር አካላት ጋር በመሆን ምቹ የኢኖቬሽን ከባቢን መፈጠር የሚያስችል የጤና ኢኖቬሽን ማበልጸጊያ ማዕከል በቅርቡ ሥራ ይጀምራል።
ይህም ማዕከል በዓለም አቀፍ እንዲሁም በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚገጥሙ ችግሮችን ተቋቁሞ ማለፍ የሚችል የጤና ስርዓት ለመዘርጋት እንደሚያስችል አንስተዋል።
ይህንን እና ሌሎች መሰል የኢኖቬሽን ሥራዎችን ለማገዝ፣ በፋይናንስ አቅርቦቱ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት ስታርት አፕ እድገት ተቋማዊና ሕጋዊ አሠራርን የሚዘረጋ ረቂቅ አዋጅ ማዘጋጀቱን አስታውሰዋል።
ረቂቅ አዋጁ የኢኖቬሽን ነባር አሠራሮችን፣ የምርትና የአገልግሎት ሂደቶችንና ምርቶችን በሳይንሳዊ መንገድ በመቀየር ሰዎች ሕይወታቸውን በተሻለ መንገድ እንዲመሩ የሚያደርግ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ይህን ሥርዓት መፍጠር ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂን ከማስረጽ፣ በተለይም ለወጣቶች የሥራ ዕድል የመፍጠር አቅሙም ከፍተኛ የሆነ እንዲሁም፤ በአገር የኢኮኖሚ ዕድገት ላይ ሊያመጣ የሚችለውን ለውጥ ታሳቢ በማድረግ የሕግ ማዕቀፍ ለመፍጠር አስፈላጊ መሆኑንም ጠቁመዋል።
"ኢኖቬሽን ቅንጦት አይደለም" ያሉት ደግሞ የሚኒስቴሩ ሚኒስትር ዴኤታ ባይሳ በዳዳ ሲሆኑ፤ "ለሀገር ብሎም ለጤናው ዘርፍ እስካሁን በሚፈለገው ልክ ያልተሰሩ የጤና ተደራሽነት አገልግሎት፣ ጥራት፣ እኩልነት እና የታካሚ ደህንነትን ማረጋገጫ ነው" ብለዋል።
የጤና ሚኒስቴር ኢትዮጵያ ከምትከተለው ሳይንስ ኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ፖሊሲ ጋር የጤናውን ዘርፍ በማናበብ የአምስት ዓመት ስትራቴጂ እቅድ ማዘጋጀቱን የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታው፤ "ይህ ስትራቴጂ ወጥ የሆነ አሰራርን በመፍጠር ሥራዎች ውጤታማ እንዲሆኑ ያደርጋል" ብለዋል።
"ስትራቴጂው ቀድሞ የነበረው አሰራር የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በሚሰራቸው የተበታተኑ ሥራዎችን በአንድ ወጥ የሆነ አሰራር እንዲኖር ያስቻለ ነው" ሲሉም ገልጸዋል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
ብሔራዊ የጤና ኢኖቬሽን ማበልጸጊያ ማዕከል በቅርቡ ስራ እንደሚጀምር ተገለጸ
የጤናውን ዘርፍ ከሳይንስ፣ ኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ፖሊሲ ጋር ያስተሳሰረ የአምስት ዓመት ስትራቴጂ እቅድ መዘጋጀቱ ተነግሯል
